ቀጥታ፡

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ18ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 2/2015(ኢዜአ)፦ በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር የአራተኛና የመጨረሻ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳሉ።

በዚህም ሀድያ ሆሳዕና ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ይጫወታሉ።

ሀድያ ሆሳዕና በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በ24 ነጥብ 7ኛ እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ በ21 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ሀድያ ሆሳዕና በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን ሶስት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዶ አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ ካለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች አንዱን ሲያሸምፍ በአራቱ ሽንፈት አስተናግዷል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕና 3 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በሌላኛው የሊጉ መርሐ-ግብር ለገጣፎ ለገዳዲ ከኢትዮጵያ መድን ጋር ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ለገጣፎ ለገዳዲ በዘጠኝ ነጥብ 16ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ኢትዮጵያ መድን በ33 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ለገጣፎ ለገዳዲ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን በአራቱ ሽንፈት ገጥሞታል።

ተጋጣሚው ኢትዮጵያ መድን ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች መካከል ሶስቱን ሲያሸንፍ አንዱን በሽንፈት እንዲሁም አንዱን ደግሞ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን 4 ለ 1 በሆነ ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል።

በተያያዘ ዜና ትናንት በተደረጉ 18ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ሐዋሳ ከተማ አዳማ ከተማን 2 ለ 0 ሲያሸንፍ ኢትዮ ኤሌክትሪክና ወላይታ ዲቻ በአንጻሩ አንድ አቻ ተለያይተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም