ቀጥታ፡

የክልሉን ልዩ ኃይል መልሶ የማደራጀቱ ስራ በመጠናቀቅ ላይ ነው--የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል

 

አዲስ አበባ ሚያዝያ 1/2015(ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ልዩ ኃይሉን መልሶ የማደራጀቱ ስራ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን የክልሉ ሠላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።

ወደ ተግባር የተገባው የክልሉን ልዩ ኃይል መልሶ የማደራጀት ሥራ በመገባደድ ላይ እንደሚገኝ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት የሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ ገልጸዋል፡፡

ኃላፊው የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀቱ ስራ እንደሀገር ለውጡን ተከትሎ የተለያዩ ጥናቶች እየተካሄዱ የቆዩ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የክልሉ ልዩ ኃይል ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን በመሆን እንደ ሀገር ተደቅኖ የነበረውን የህልውና አደጋ በመቀልበስና በአንዳንድ አካባቢዎች ተከስተው የነበሩ የጸጥታ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለ መቆየቱንም አንስተዋል።

ልዩ ሃይሉ አሁን ክልሉ ላይ ለተገኘው ሠላም ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው እንደሀገር በተከናወነው ጥናትና መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ልዩ ሃይሉን መልሶ ማደራጀት የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በዚህ መሰረትም የልዩ ሃይል አባላት እንደ ምርጫቸው እንደገና የማደራጀት ስራው እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

በክልል ደረጃ በፖሊስ ኮሚሽን የተዋቀረው የመልሶ ማደራጀት ኮሚቴ ከሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል አካላት ጋር በመሆን የማደራጀት ስራ እየሰራ ነው ብለዋል።

የቢሮ ኃላፊው የክልሉን ልዩ ኃይል መልሶ ለማደራጀት በሚደረገው ተግባር ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም