በአትሌቲክስ በዓለም የስመ ጥር አትሌቶች መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ በዘርፉ ዳኝነት ግን ተሳትፎዋ ዝቅተኛ ነው- የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን - ኢዜአ አማርኛ
በአትሌቲክስ በዓለም የስመ ጥር አትሌቶች መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ በዘርፉ ዳኝነት ግን ተሳትፎዋ ዝቅተኛ ነው- የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን

አዲስ አበባ ሚያዚያ 1/2015(ኢዜአ)፦በአትሌቲክስ በዓለም የስመ ጥር አትሌቶች መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ በዘርፉ ዳኝነት ግን ተሳትፎዋ ዝቅተኛ መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ገለጸ።
ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ስፖርት የአሸናፊነትና ድል አብሳሪ ጀግና አትሌቶችን እያፈራች የቀጠለችና በዘርፉ በክብር ዙፋን ላይ ከተቀመጡ ጥቂት የዓለም አገራት አንዷ ናት።
በዓለም አትሌቲክስ ታሪክ አበበ ቢቂላ፣ ምሩጽ ይፍጠር፣ ማሞ ወልዴ፣ ፋጡማ ሮባ፣ ደራርቱ ቱሉ፣ ሀይሌ ገብረስላሴ ፣ቀነኒሳ በቀለ፣ ጌጤ ዋሜ፣ጥሩነሽ ዲባባ ፣ገንዘቤ ዲባባ ሌሎች አትሌቶች በትውልድ ቅበብሎሽ ኢትዮጵያን እያስጠሩ ቀጥለዋል።
በአትሌቲክስ የውድድር መድረክ በዓለም ስሟ ደጋግሞ የሚያነሳውን ያክል በዘርፉ በዳኝነትና ሌክቸረርነት ግን ተሳትፎዋ ለምን ዝቅተኛ ሆነ ሲል ኢዜአ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽንን አነጋግሯል።
በፌዴሬሽኑ የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክተር ሳሙኤል ብርሃኑ፤ በዓለም የስመ ጥር አትሌሎች መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ በዘርፉ ዳኝነት አሁን ላይ የሚወክሏት ሁለት መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።
በመሆኑም ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ተወዳዳሪነት በዓለም ያላትን ውጤት ያክል በዳኝነት ተሳትፎም ለማሳካት ምን እየተሰራ ነው በማለት ኢዜአ ከአቶ ሳሙኤል ብርሃኑ ጋር ቆይታ አድርጓል ።
ኢዜአ - ኢትዮጵያ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ሻምፒዮን በመሆን ስማቸውን በወርቅ ቀለም የጻፉ በርካታ አትሌቶች ያፈራች ሀገር ናት፤ እነዚህ አትሌቶች ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ ከመውጣታቸው በፊት በሀገር ውስጥ አቅማቸውን የሚፈትሹበትና ሀገራቸውን የሚወክሉ ስፖርተኞች የሚመለመሉበት የሀገር ውስጥ ውድድሮች ይዘጋጃሉ፣ በእነዚህ የሀገር ውስጥ ውድድሮች የሚመሩ ብቁ የሆኑ ዳኞችና ሌሎች ባለሙያዎች በማፍራት በኩል ፌዴሬሽኑ እየሰራቸው ያሉ ተግባራት ምን ይመስላሉ ፤ምን ያህል የአትሌቲክስ ዳኞችስ አሉ ?
አቶ ሳሙኤል -በራሱ ወጪ በርካታ ዳኞችን በማፍራትና ስልጠና በመስጠት ረገድ ምን አልባት በአፍሪካ ሪጅናል ዲቨሎፕመንት ሴንተር አጠገባቸው ካሉ እንደ እንደ ደቡብ አፍሪካና ኬኒያ ቀጥሎ እኛ ነን ያለነው። በተለይ በፊት ሁለተኛ ደረጃ ይባል የነበረ አሁን ግን በአዲሱ አደረጃጀት አንደኛ ደረጃ ተብሎ ከህጻናት አትሌቲክስ እስከ መልቲ ኢቭንት ወይም ደግሞ ደረጃ አንድ ተብሎ በሚባለው ደረጃ ወደ 220 አካባቢ አሰልጣኞች አሉን። ከዚህ ባለፈ ዳኞችም እንደዚሁ ከ240 ገደማ አካባቢ ዳኞች አሉን በዓለም አቀፍ ደረጃ አንደኛ ደረጃ የወሰዱ ናቸው። ሁለተኛ ደረጃ እና ከዚያ በላይ የሆኑ ደግሞ ወደ 40 ያሉ ሲሆን ወደ 14 የሚሆኑ አሰልጣኞች ስፔሻላያዝድ ያደረጉ ዳኞች አሉን።
ኢዜአ -የባለሙያዎች የስልጠና እና የልህቀት ማዕከለት በእነሱ ሀገር መኖሩ ባለሙያዎች በማፍራት በኩል ከሌሎች ሀገራት የተሻለ እድል ያገኛሉ ማለት ነው ?
አቶ ሳሙኤል _ እነሱ እዚያው የስልጠና ሴንተር አጠገባቸው በመሆኑ በብዙ ነገሮች የተሻለ ባለሙያ የማፍራት እድል አላቸው። ለምሳሌ ኬኒያ ላይ ያለው የአትሌቲክስ ዲቭሎፕመንት ሴንተር ስትመለከት የተቋቋመው ለኬኒያዊን ብቻ ሳይሆን እንግሊዘኛ ተናጋሪ ለሆኑ የአፍሪካ ሀገራት እንዲሰጠልጥኑበት ተብሎ ነው። ሴኔጋል ያለውም ለፈረሳይኛ ተናጋሪዎች የተዘጋጀ ኤኤዲሲ ሪጅናል ዲቨሊምፕመንት ሴንተር አለ፤ እነ አልጀሪያ ቱኒዚያና መሰል ፈረሳንይኛ ተናጋሪ የአፍሪካ ሀገራት ተብሎ የተዘጋጀ ነው። በእነዚህ ሀገራት ስልጠናዎች ሲዘጋጁ ለእነሱ ቅርባቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከሌሎች ሀገራት የተሻለ እድል አላቸው። አንዳንዴ ሌሎች ሀገራት በተለያየ ምክንያት መሳተፍ ሳይችሉ ሲቀርም ጭምር ስልጠናውን የመወሰድ ሰፊ እድል አላቸው። ለዚያ ነው እኛ ሁለት ወይም ሶስት ሰው ስናሰለጥን እነሱ ስድስት ሰባት ስዎችን የማሰልጠን እድሉ አላቸው እና ከዚህ ጋር ተያየዞ ቁጥራቸው በዛ ያሉ አሰልጣኞች ቁጥራቸው በዛ ያሉ ዳኞችና ሌክቸረሮች አሏቸው ።
ኢዜአ -የአትሌቲክስ ባለሙያዎች በማፍራት በተጨማሪ የሰለጠኑትን በመጠቀም የተወሰነ ችግሮች እንዳሉ ይነሳል የሰለጠኑ ባለሙያ በአግባቡ መጠቀም ላይ ያሉ ክፍተቶች ምንድ ናቸው ?
አቶ ሳሙኤል- እንደ አጠቃላይ ሲታይ ኢትዮጵያ በባለሙያ ረገድ ቁጥሩ በዛ ያለ ባለሙያ በማፍራት ላይ ነች። ነገር ግን ፌዴሬሽኑ ብዙ ወጪ አድርጎ ስልጠናዎችን ከተከታተሉ በኋላ በአግባቡ እየተጠቀሙበት ያሉት ጥቂት ክልሎችና ማናጀሮች ካልሆኑ በስተቀር ሰው በሰለጠነው ልክ እየተጠቀመበት አይደለም ወረቀቱን ወስዶ ዝም ብሎ የማስቀመጥ አይነት ነገር አለ።
ኢዜአ- አሁን ላይ ከሀገር ውስጥ አልፈው በሌሎች በአፍሪካና ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚሳተፉ ዳኞች አሏት ?
አቶ ሳሙኤል - አሁን ላይ በኛ ሀገር ሁለት ዳኞች አለን በእርምጃ ላይ ንጉሴ ጌቻሞና በሌላው ላይ ደግሞ እኔ አለሁኝ እኔ አሁን በሶስተኛ ደረጃ የሚባለው ወይም ሴኔጋል ላይ ሄደን ሴሚናሩን ወስጄ አጠናቅቄለሁ። በዚህም ዓለም ሻምፒዮና እና ለኦሊምፒክም አትሌቲክስ ውድድሮች ከሚዳኙ ግሩፕ ውስጥ ነው ያለሁት ።
ኢዜአ - ከዳኞች በተጨማሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለሙያ ማፍረት ሲነሳ የሌክቸረሮች ጉዳይ አብሮ ይነሳልና ኢትዮጵያ ምን ያህል የአትሌቲክስ ስፖርት ስልጠና የሚሰጡ ሌክቸረሮች አሏት ?
አቶ ሳሙኤል- በአጋጣሚ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለነው ሶስት ሌክቸረሮች ነው ያለነው።
ኢዜአ- በዓለም አቀፍ ደረጃ ዳኝነትና ሌክቸርረነት ያሉ ኢትዮጵያዊን ባለሙያዎች ቁጥር ሀገር ውስጥ ካለው ብዙ ቁጥር አንፃር ዝቅተኛ የሆነበት ምክንያት ምንድን ነው መፍትሄውስ ?
አቶ ሳሙኤል -እኛ አገር ያሉ ባለሙያዎች ትልቁ ችግር ቋንቋ ነው፣ የሌክቸረርነት ስልጠና ኬኒያ ላይ ሄዲህ ነው የምትወስደው እና ስልጠናውን የምትወስደው ከተለያዩ ሀገራት ከመጡ ባለሙያዎች ጋር ስለሆነ ምዘናውን ከፍተኛ ነው።አፋችንን በፈታንበት የሀገር ውስጥ ቋንቋ የሆኑት አማረኛ ኦሮሞኛና ሌሎች ቋንቋዎችም እዚያ ጋር የለም። 100 ፐርሰንት የሚሰጠው በእንግሊዘኛ ቋንቋ ነው፤ በተግባር ሁሉ የተሻለ ብትሆን የበለጠ ዋጋ ያለው ግን ይሄ ሰው ሌክቸረር ሆኖ ሲመደብ ሀገሩ ላይ እንዲሰራ ብቻ ታስቦ ሳይሆን አፍሪካ ሀገሮች ላይ ሁሉ እየሄደ እንዲሰጥ ታስቦ ስለሆነ የሚታየው የእንግሊዘኛ የቋንቋ ችሎታ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ብዙ ስዎች ስልጠናውን ወስደዋል ግን ማለፍ አልቻሉም። እዚያ ስትሄድ የምትወዳደረው በእንግሊዘኛ ተናጋሪ ከሆኑ መድረክ ላይ በመሆኑ በአመዛኙ የእኛ ተግዳሮት የሚሆነው የብዙዎቻችን ችግር የሚሆነው ቋንቋ ነው። እዚህ ላይ መስራት አለብን ፤እኔ ጋር ባለው መረጃ ቋት ከ15 እና 16 በላይ ስዎች ሂደው ወድቀው የመጡ ስዎች አሉ ማለት የሚገባውን ውጤት ሳያገኙ የመጡ ስዎች አሉ፤በአሰልጣኝነት ደረጃ ብናይም እኔ አስከማውቀው ትቂት አሰልጣኞች ውጭ ሀገር ኮንትራት ወስደው ለማሰልጠን የሞከሩ ነበሩ ግን አብዛኞቹ ከሀገር ውሰጥ ብቻ የተወሰኑ ናቸው ለዚህም አንዱ የአቅም ጉዳይ ሲሆን ሌላው የቋንቋ ችግርም አለበት። ስለዚህ ቀጣይ አሰልጣኞች አቅማቸውን ማጎልበትም የሚጠይቅ ቢሆንም በዳኞችና ሌክረሮች ላይ ግን የእንግሊዘኛ ቋንቋ ችሎታን ማዳበር ላይ መስራት አለባቸው
ኢዜአ _ስለነበረን ጊዜ አመሰግናለሁ
አቶ ሳሙኤል- እኔም አመሰግናለሁ