ቀጥታ፡

ዶክተር አለሙ ስሜ በህዝብ ትራንስፖርት መስጫ ተርሚናሎች ውስጥ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ተዘዋውረው ተመለከቱ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 1/2015 (ኢዜአ) የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ በህዝብ ትራንስፖርት ተርሚናሎች ውስጥ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ተዘዋውረው ተመለከቱ።


 

ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት በትራንስፖርት ስምሪት መስጫ ሰአት ተገኝተው ምልከታ ያደረጉት በላምበረት እና አዲስ ከተማ የህዝብ ትራንስፖርት በሚሰጥባቸው ተርሚናሎች ነው፡፡


 

ዶክተር አለሙ ስሜ ባደረጉት ድንገተኛ ምልከታም በተርሚናሎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

በዚህም የስምሪት አሰጣጥ ስርዓትን፣ የተሳፋሪዎች መስተንግዶ እና አያያዝን፣ የትራንስፖርት ታሪፍ ተግባራዊነትንና አገልግሎቶች ህብረተሰቡን በሚመጥን እና እርካታን በሚያረጋግጥ መልኩ አገልግሎት እየተሰጡ መሆኑን ፈትሸዋል፡፡


 

የሚሰጡ አገልግሎቶችን በተመለከተም በተርሚናሎች ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች አገልግሎት የሚሰጡ አደረጃጀቶችን እና ተሳፋሪዎችን ማነጋገራቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡


 

በዚህም ሚኒስትሩ ያስተዋሏቸው የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶች በአስቸኳይ እንዲስተካከሉ ማሳሰባቸውንና በቀጣይም በተርሚናሎች የሚሰጠው የህዝብ ትራንስፖርት ስምሪት አገልግሎት በጥብቅ ክትትል እንደሚመራ ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም