የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 1/2015(ኢዜአ)፦ በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር የሶስተኛ ቀን ውሎ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
አዳማ ከተማ ከሐዋሳ ከተማ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አዳማ ከተማ በ24 ነጥብ 8ኛ እንዲሁም ሐዋሳ ከተማ በ25 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
አዳማ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፎ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።
ተጋጣሚው ሐዋሳ ከተማ በበኩሉ ካደረጋቸው አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች መካከል አንዱን በማሸነፍ አራት ጊዜ በአቻ ውጤት ተለያይቷል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ አዳማ ከተማ 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
በሌላኛው የሊጉ መርሐ-ግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከወላይታ ዲቻ ጋር ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በስምንት ነጥብ 16ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ላይ የሚገኝ ሲሆን ወላይታ ዲቻ በበኩሉ በ20 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች አራት ጊዜ ተሸንፎ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።
ተጋጣሚው ወላይታ ዲቻም እንዲሁ ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ተሸንፎ ሶስት ጊዜ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ መለያየታቸው ይታወሳል።
በተያያዘም ትናንት በተደረጉ 18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ቡና ወልቂጤ ከተማን 1 ለ 0 እንዲሁም ባህር ዳር ከተማ ፋሲል ከነማን 2 ለ 1 ማሸነፋቸው ይታወሳል።