ቀጥታ፡

ሕዝበ ሙስሊሙ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለመደገፍ የሚያደርገውን ጥረት ማጠናከር አለበት - ሸኽ ሃጂ ኢብራሂም 

አዲስ አበባ መጋቢት 30/2015 (ኢዜአ)፦ ሕዝበ ሙስሊሙ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለመደገፍ የሚያደርገውን ጥረት ማጠናከር አለበት ሲሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸኽ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ ተናገሩ።

  ሦስተኛው ዙር ታላቁ የጎዳና ላይ የኢፍጣር ሥነ-ሥርዓት “ኢፍጣራችን ለወገናችን” በሚል መሪ ኃሳብ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸኽ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ በዚሁ ጊዜ  ባስተላለፉት መልዕክት ስናፈጥር የተቸገሩ ወገኖችን በማሳብና በመረዳዳት ሊሆን ይገባል ብለዋል። 

ሕዝበ ሙስሊሙ ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ለመርዳት እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል። 

ዛሬ የተደረገው የጎዳና ላይ ኢፍጣር አንድነትና አብሮነትን ለማጠናከር ሰላምና ፍቅርን ለማጽናት እንደሚያግዝ ተናግረዋል። 


 

የጎዳና ላይ ኢፍጣር አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ፈይሰል ከማል በበኩላቸው መርሃ ግብሩ አንድነትን፣ መሰባሰብን፣ ሰላምን በማሳየት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በአደባባይ ላይ በጋራ ማፍጠር የእርስ በእርስ ትስስርን ለማጎልበት ጠቃሚ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተለያየ ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ወገኖች ድጋፍ ለማሰባሰብና አብሮነትን ለማሳየት እንደሆነም ተናግረዋል።

የጎዳና ላይ ኢፍጣር በቀጣይ ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ ለአገር ገጽታ ግንባታ እንዲውል የሁሉም ድጋፍ እንደሚሻ አስገንዝበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም