ቀጥታ፡

ተመራቂዎች ሕዝቦችን የሚያስተሳስሩ እሴቶች ለማጠናከር የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል - የሰላም ሚኒስቴር

ሆሳዕና  መጋቢት 30/2015( ኢዜአ)፡- ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተመራቂዎች ሕዝቦችን የሚያስተሳስሩ ማህበራዊ መሰረቶችን በማጉላት ለዘላቂ ሰላምና ለአገር ግንባታ መረጋገጥ የበኩላቸውን ሚናቸውን  መወጣት እንደሚጠበቅባቸው  የሰላም ሚኒስቴር አሳሰበ።

የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ በስድስተኛው  ዙር ተቀብሎ ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ የሚጠጉ የብሔራዊ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰልጣኝ ወጣቶች ዛሬ አስመርቋል።


 

የሰላም ሚንስትር አማካሪ አምባሳደር እሸቱ ደሴ እንዳሉት፤ተመራቂዎቹ ለሕብረ ብሔራዊ አንድነትና በዘላቂ የሀገር ግንባታ ሂደት  ሚናቸውን  መጫወት ይጠበቅባቸዋል።

ጠንካራ አገር ለመገንባት በሚደረገው ሂደት ውስጥ ጠንካራ ብሔራዊ መግባባት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፣ ለዚህ ደግሞ የውስጥ ሰላምን ማጠናከር ከሁሉም ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው ብለዋል።

''የሰላምን ዋጋ ማወቅ የሚቻለው ሰላም በጠፋ ጊዜ ነው'' ሲሉ የገለጹት አምባሳደር እሸቱ፣ ተመራቂዎቹ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ በውይይት መፍታትና በመሰል መስኮች የተሰጣቸው ስልጠና ወደ ተግባር በመመንዘር ለሰላም ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል።

''የሰላም ግንባታ ልክ እንደ ጦር ግንባር ጀግንነትን ይፈልጋል'' ያሉት አምባሳደሩ፤ ትውልዱ ለአገራዊ ውበት ልዩ አቅም የሆኑትን ብዝሃ ማንነቶች በማጉላትና ሕብረ ብሄራዊ አንድነትን ለማጠናከር በዘላቂ የአገር ግንባታ ሚናቸውን መጫወት እንደሚኖርባቸውም ነው ያሳሰቡት።

በተለይም ወደ ማህበረሰቡ በሚገቡበት ወቅት የባህል ልውውጥ ከማድረግ ባለፈ፤ሕዝቦችን በሚያስተሳስሩ ማህበራዊ መሰረቶች ላይ በማተኮር ለአገራዊና ዘላቂ ሰላም ግንባታ ሂደት መሳተፍ እንዳለባቸው አሳስበዋል።  

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መኪዬ መሐመድ፤  መንግስት ብሔራዊ መግባባትን ለማጠናከር በቅድሚያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በመስራት ላይ  እንደሚገኝ ገልጸዋል።

እንደ አገር የተጀመረው የሁለንተናዊ ብልጽግና ጉዞ ከግብ ለማድረስ ወሳኙ ሰላምን ማረጋገጥ መሆኑንና ለዚህም መንግስት ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም ርብርብ በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል።

የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት መከፋፈልና መጠራጠርን በማስወገድ ኢትዮጵያዊ እሴቶችን አስጠብቆ በማስቀጠል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው ተመራቂዎች ይህን በተግባር ማሳየት እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል። 

የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ፀደቀ ላምቦሬ፤ ዩኒቨርሲቲው ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሁለት ሺህ የሚጠጉ ብሔራዊ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን ከአንድ ወር በላይ ማሰልጠኑን ገልጸዋል።

ስልጠናው ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ምሩቃን የተሳተፉበት በመሆኑ ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅ የሆኑ መልካም እሴቶችን ለማስተዋወቅና ለመጠበቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ከፍታ የሚረጋገጠው ዜጎቿ በጋራና በአንድነት መጓዝ ሲችሉ ነው ያሉት ዶክተር ፀደቀ፣ ተመራቂዎቹ ለአብሮነት እሴቶች መጠናከር  ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የሰላም ሚኒስቴር ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ከ34 ሺህ በላይ ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰልጣኞችን አሰልጥኖ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ማሰማራቱ በምርቃቱ ስነ ስርዓት ላይ ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም