ቀጥታ፡

የዩንቨርሲቲዎችን ራስ ገዝነት የሚደነግገው ረቂቅ አዋጅ ነጻነትን ከተጠያቂነት ጋር የሚያሰፍን ሆኖ ይዘጋጃል  - ዶክተር ነገሪ ሌንጮ

አዲስ አበባ መጋቢት 30/2015 (ኢዜአ)፦   ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝነት የሚደነግገው ረቂቅ አዋጅ ነጻነትን ከተጠያቂነት ጋር የሚያሰፍን ሆኖ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት ልማት ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ገለጹ።  

የዩኒቨርሲቲዎች የራስ ገዝ አስተዳደር ረቂቅ አዋጅን በሚመለከት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች ጋር የግብዓት ማሰባሰቢያ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት አገርን በመገንባት ሂደት ምሁራን የመሪነቱን ሚና ሊወጡ ይገባል።

ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ የሚያሻግር ትውልድ ማፍራት ላይ በትኩረት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

ይህን ለማሳካት ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት፣ አገርን የሚጠቅም ምርምር ለማካሄድም የትምህርት ተቋማት ጥራትን መሰረት ያደረገ አደረጃጀትን መከተል እንዳለባቸው አንስተዋል።

በረቂቅ ደረጃ ያለው አዋጅ ነጻነትን ከተጠያቂነት ጋር የሚያሰፍን ሆኖ እንደሚዘጋጀም አመላክተዋል።

በቀጣይ በሚደረጉ ውይይቶች ተሻሽሎ የማንንም ጥቅም በማይጎዳ መልኩ እንደሚዘጋጅም ነው የተናገሩት።


 

የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የምክክር መድረክ የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ማድረግ ያስፈለገው ተቋማዊና አስተዳደራዊ ነጻነት እንዲኖራቸው መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ላይ ያለው አሰራር በሲቪል ሰርቪስ በወጡ መመሪያዎች መሆኑ ለዩኒቨርሲቲዎች የትምህርትና ተቋማዊ ነጻነት ምቹ አለመሆኑን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር፣ በትምህርት፣ በማኅበረሰብ ለውጥ ልቀው እንዲወጡ የአስተዳደር ነጻነት ዋነኛው መሆኑን አመላክተዋል።

ረቂቅ አዋጁ ዩንቨርስቲዎች የተሻለ ተልዕኮ ይዘው በይበልጥ እንዲሰሩ የሚያበረታታ መሆኑን ጠቁመዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ የዩንቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች አዋጁ ዩንቨርሰቲዎችን የሚያሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም በአስተዳደር ላይ ያለውን ተግዳሮት በመቅረፍ ረገድ ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም