አስተማማኝ ሰላምን አስፍኖ አገርን ለማጽናት በአንድነትና በመተማመን መንፈስ መስራት ይገባል - አቶ ታዬ ደንደአ - ኢዜአ አማርኛ
አስተማማኝ ሰላምን አስፍኖ አገርን ለማጽናት በአንድነትና በመተማመን መንፈስ መስራት ይገባል - አቶ ታዬ ደንደአ
ጅማ መጋቢት 30/2015 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላምን አረጋግጦ አገርን ለማጽናት በአንድነትና በመተማመን መንፈስ መስራት ከሁሉም እንደሚጠበቅ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ ገለጹ።
በሰላም ሚኒስቴር አስተባባሪነት በጅማ ዩኒቨርሲቲ በ6ኛው ዙር ብሔራዊ የማህበረሰብ በጎ ፍቃድ አገልግሎት ለአንድ ወር የሰለጠኑ 1 ሺህ 600 ወጣቶች ተመርቀዋል።
የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያውያን በሁሉም መስክ ወደፊት ለማምጣት ከሁሉም በላይ ሰላም ወሳኝ ነው።
በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም ገንብቶ አገርን ለማጽናት ሁሉም በአንድነትና በመተማመን መንፈስ ለዘላቂ ሰላም መትጋት እንደሚገባ ገልጸዋል።
"አገራዊ ለውጡን አጠናክሮ ለማስቀጠልና የአገር ግንባታ ሚናችንን ስኬታማ ለማድረግ በመተማመንና በአንድ ልብ በጋራ መስራት አለብን" ብለዋል።
"ለወጣቶቹ የተሰጠው የአብሮነት ስልጠና ለሰላምና ለብሔራዊ መግባባት ጉልህ ሚና ያበረክታል" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በተሰጠው ስልጠና 41 ሺህ ወጣቶች መሳተፋቸውን ገልጸዋል።
ስልጠናቸውን የተከታተሉ ወጣቶች የተማሩትን ለሌሎች ማሳወቅ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የማህበረሰብ በጎ ፍቃድ አገልግሎት በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የበጎ-ፍቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶችን በብዛት ለማፍራት እያስቻለ መሆኑን አመልክተዋል።
በተለያዩ ዙሮች ስልጠናውን ያገኙ ወጣቶቹ የአመለካከት፣ የበጎ አድራጊነት፣ የስራ ተነሳሽነትና ፈጣሪነትን ክህሎት እንዲያገኙ በመደረጉ ሕብረተሰቡን የሚጠቅሙ ስራዎችን እያከናወኑ ነው ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው።
"በተለያዩ አካባቢዎች ጭምር በመሄድ የበጎ ፍቃድ ሥራዎችን ከማከናወን ባለፈ የተለያዩ ባህልና ቋንቋዎችን በመልመድ አብሮነትን እያጠናከሩ እንደሆነም አክለዋል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ነጻነት ወርቅነህ በበኩላቸው፣ ተቋሙ በበጎ ፍቃድ ስራዎች ተሳትፎዎችን እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ባለፋት ስድስት ተከታታይ ዙሮች በሰላም ሚኒስቴርና በዩኒቨርሰቲው ትብብር ከ12 ሺህ በላይ ወጣቶች በብሔራዊ የማህበረሰብ በጎ-ፍቃድ አገልግሎት መሰልጠናቸውን ተናግረዋል።
"ወጣቶች አገር የምትገነባው ሰላምን መሰረት ባደረገ ውይይት፣ ንግግርና መግባባት መሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል" ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ሁሌም የንግግርና የመደማመጥ ባህልን ማጎልበት ለአብሮነት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው ስልጠናውን ተከታትለው የተመረቁ ወጣቶች በበኩላቸው በቆይታቸው ለቀጣይ ሕይወታቸው የሚጠቅም በርካታ ልምድና እውቀቶችን ማግኘታቸውንና አገራቸውን ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።