ለሽግግር ፍትህ መሳካት ድርሻችንን እንወጣለን- የኢትዮጵያ የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባኤ - ኢዜአ አማርኛ
ለሽግግር ፍትህ መሳካት ድርሻችንን እንወጣለን- የኢትዮጵያ የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባኤ
አዳማ መጋቢት 30 /2015(ኢዜአ)፡- ለሽግግር ፍትህ መሳካትና ለሰላም ግንባታ የድርሻውን እንደሚወጣ የኢትዮጵያ የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባኤ አስታወቀ።
የመማክርት ጉባኤው ከጀስቲስ ፎር ኦል ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር "በፍትህ ሽግግርና በሰላም ግንባታ የሀገር ሽማግሌዎች ሚና " በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ የሰላም ምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል ።
የኢትዮጵያ የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባኤ ሰብሳቢ ዶክተር ተስፋፅዮን ደለለው፤ በሀገራችን ለነበሩ አለመግባባቶችና ችግሮች መፍትሔ በመስጠት ረገድ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎች ሚና የጎላ ነው ብለዋል ።
ግጭቶች እንዲወገዱና የህዝቦች አንድነት እንዲጎለብት በሽግግር ፍትህና በሰላም ግንባታ ሂደት ላይ የሀገር ሽማግሌዎች ሚናችንን መወጣት አለብን ሲሉም ገልጸዋል።
በተለይ ለተጎዱ ወገኖች የእርቅና የሰላም መፍትሔ ይዘን መቅረብና ወደ ነበሩት ሰላማዊ ህይወት እንዲመለሱ ማስቻልም አለብን ብለዋል ።
በየደረጃው የሚገኙ ሁሉም የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና የሃይማኖት መሪዎች በሽግግር ፍትህና በሀገር ሰላም ግንባታ ላይ አስተዋጿቸውን እንዲጠናከሩ በመደገፍ የመማክርት ጉባኤው የድርሻውን እንደሚወጣ አሰታውቀዋል።
የጀስቲስ ፎር ኦል ኢትዮጵያ ፕሬዚንዳንት ፓስተር ዳንኤል ገብረስላሴ በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ አለመግባባቶችን መፍታት ለመንግሥት ብቻ የሚተው ሳይሆን ሁላችንም የድርሻችንን የምንወጣበት ነው ብለዋል ።
በተለይ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች፣ ሃዳ ሲንቄዎችና የሃይማኖት መሪዎች እርቅን ለማውረድና ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ግንባር ቀደም ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
የሰላም አጀንዳዎችንን በሁሉም ክልሎች ተደራሽ በማድረግ ግጭቶችን አጀንዳ የሚያደርጉትን አካላት ለማስተካከል በሚካሄደው እንቅስቃሴዎች ውስጥ የድርሻችንን መወጣት አለብን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በእኩልነት የመሰረቷትና በአንድነት ለዛሬው ትውልድ ያበቋት ታላቅ ሀገር መሆኗን ያወሱት ፓስተር ዳንኤል፤ ታላቅነቷን በማስቀጠል ረገድ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና የሃይማኖት መሪዎች የድርሻቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
በምክክሩ ላይ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣አባገዳዎች፣ሃዳ ሲንቄዎችና የሃይማኖት መሪዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ ።