የብልፅግና ፓርቲ የወጣቶች ሊግ ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ የህዳሴ ግድብ የቦንድ ግዥ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር በድሬዳዋ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የብልፅግና ፓርቲ የወጣቶች ሊግ ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ የህዳሴ ግድብ የቦንድ ግዥ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር በድሬዳዋ እየተካሄደ ነው
ድሬዳዋ፤ መጋቢት 30 / 2015 (ኢዜአ)፡- የብልፅግና ፓርቲ የወጣቶች ሊግ ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል የቦንድ ግዥ ንቅናቄ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር በድሬዳዋ እየተካሄደ ነው።
በፓርቲ የድሬዳዋ የጥናትና ምርምር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ ታደሰ መርሃ ግብሩን ሲያስጀምሩ፤ የሀገሪቱ ወጣቶች ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ በጉልበት፣ በዕውቀትና በገንዘብ እያደረጉት ያለው ርብርብ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
በድሬዳዋ ዛሬ የተጀመረው ሀገር አቀፍ የቦንድ ግዥ ንቅናቄ ይህን ወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግረው እንደሆነም ገልዋል።
ወጣቱ የጀመረውን ሁሉን አቀፍ የልማት ተሳትፎ አጠናክሮ ደማቅ አሻራውን በማኖር ሀገዊ የለውጥ ሂደቱ ዳር ማድረስ ላይ መረባረብ እንዳለበትም አሳስበዋል።
የብልፅግና ፓርቲ የወጣቶች ሊግ ምክትል ፕሬዝዳንትና የጽህፈት ቤት ኃላፊ ወጣት አባንግ ኩመድ በበኩሏ፤ የግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሊጉ አባላቱን በማስተባበር የራሱን አሻራ በማሳረፍ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው ብላለች።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በተዘጋጀውና ለአንድ ወር በሚዘልቀው ንቅናቄ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ወጣቶችን በማሳተፍ የግማሽ ቢሊዮን ብር የቦንድ ግዥ ለመፈፀም መታቀዱንም አስታውቃለች።
የዚህ ታላቅ ታሪክ ባለቤት መሆን የሚያኮራ መሆኑን የገለጸችው ወጣት አባንግ፤ የግድቡን ቀሪ ግንባታ ከዳር ለማድረስ ወጣቱ ባለው አቅም ለመሳተፍ ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ መሆኑን ተናግራለች ።
በድሬዳዋ ዛሬ በተጀመረው የቦንድ ግዥ ንቅናቄ ላይ ሁሉም ተሳታፊ እንዲሆንም ምክትል ፕሬዚዳንቷ ጠይቃለች።
በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ሚናን አስመልክተው የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት ደግሞ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍቅርተ ታምር ናቸው።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ፤ ወጣቱ በግድቡ ግንባታ ላይ በባለቤትነት እያደረገ ያለው ተሳትፎ የሚበረታታና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
በተለይ አሁን በድሬዳዋ በተጀመረው የቦንድ ግዥ ንቅናቄ ከመሳተፍ ባለፈ በዲፕሎማሲው ዘርፍ በዕውቀትና በቴክኖሎጂ የታገዘ ድጋፉን አጠናክረው እንዲቀጥሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመድረኩ ላይ የሁሉም ክልሎች፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤቶች ኃላፊዎች ጨምሮ ሌሎችም የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች እየተሳተፉ ነው።
ተሳታፊዎቹ ለመነሻ በቀረበው ጽሁፍ ላይ ከተወያዩ በኋላ ለመክፈቻው የተዘጋጀውን የህዳሴ ግድብ ቦንድ እስከ 20 ሚሊዮን ብር ግዥ ይፈፀማሉ ተብሎ ይጠበቃል።