ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ በነፃነት ፀንታ ትቆያለች - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ


ሁርሶ፤ መጋቢት 30 /2015(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ጀግኖች ልጆች ስላሏት በነፃነት ፀንታ ትኖራለች ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር በትምህርትና ስልጠና ዋና መመርያ ስር የሚገኘው የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ ያሰለጠናቸውን ዕጩ መኮንኖች በሁርሶ የኮንቲጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ዛሬ አስመርቋል።


 

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር ዐቢይ አህመድ በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ ጀግኖች ልጆች ስላሏት በነፃነት ፀንታ ትኖራለች ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ኢትዮጵያን የማበልፀግና የማፅናት ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።


ኢትዮጵያ ጀግኖች ስላሏት ሁሌም በነፃነትና በጀግንነት ትታያለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተመራቂ መኮንኖችም የኢትዮጵያን አይበገሬነት የማፅናትና የማስቀጠል ኃላፊነትን የገቡትን ቃል በተግባር ማረጋገጥ እንዳለባቸው በአጽንኦት አስገንዝበዋል።


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ  "ለምንም ነገር የማትቆሙ፣ ፈተና የሚያበረታችሁ እንጂ ሽብርክ የማትሉ አገርን ወደ ተሻለ ደረጃ የምታሻግሩ ናችሁ" ሲሉ ነው ተመራቂ መኮንኖቹን የገለጿቸው።


ታሪክ፣ ሃብት፣ ጀግንነትና በሁሉም መስፈርት የሚያኮራ አገር ጠባቂዎች ስለሆናችሁ እንኳን ደስ አላችሁም ብለዋል።


ጀግና ማለት  ለገባው ዓላማ እራሱን የሚሰጥ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን  ከነሙሉ ክብሯ ለትውልድ ለማስረከብ ዝግጁ መሆን ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ጀግኖች ስላሏት በነፃነት ፀንታ መቆየት ትችላለችም ብለዋል።


ተመራቂ መኮንኖች ውጊያን ጨምሮ በሁሉም ዘርፎች ለምርቃት የሚያበቃ ዝግጅትና ታላቅነትን በተግባር ያሳየንበት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚገኝበት "ጉባ" የሚለውን ስያሜን የያዛችሁ በመሆኑ ምርቃቱ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ምረቃዎች ልዩ ያደርገዋል ሲሉም ገልጸዋል።


ተመራቂ መኮንኖችም እራስን በእውቀት በማጎልበት፣ በመትጋት በመማር፣ ዘመናዊነትን በመላበስ  ለተሻለ ተግባር ራሳቸውን ለማዘጋጀት እንዲተጉም  አሳስበዋል።


የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት ትልልቅ አገራዊ ግዳጆችን በብቃት የተወጣ ሰራዊት ተገንብቷል ብለዋል። 


 

አሁንም ሠራዊቱ በስነልቦናና በአካል ብቃት ብቁ በማድረግ ማንኛውንም ግዳጅ በአኩሪ ደረጃ መፈጸም በሚያስችል ዝግጁነት ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።  

             
ሠራዊቱ አሁን ለደረሰበት ደረጃ የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ ሚና ትልቅ መሆኑን ገልጸው በቀጣይም ይሄው አስተዋጽኦው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል  አረጋግጠዋል።

 
በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ዘመናዊ ግዙፍ ሠራዊት የመገንባት ግብ ተይዞ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ግቡ እንዲሳካ አካዳሚው የድርሻውን ይወጣል ብለዋል ።


ተመራቂ መኮንኖችም በዘመናዊ አመራር እውቀት በመታገዝ ሀገርን ለማገልገል በመዘጋጀታቸው ሊደሰቱ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንደሚወጡም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።


የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ጌታቸው ዓሊ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ ለበርካታ ዓመታት ብቃት ያላቸውን መኮንኖችን አሰልጥኖ አስመርቋል ብለዋል።


ከለውጡ ማግስት በኋላም ተከታታይነት ባለው መልኩ መኮንኖቸን አሰልጥኖ እያስመረቀ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም አካዳሚው ሀገርን የሚጠብቅና የሚያሻግር ሠራዊት በማፍራት የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


ተመራቂ መኮንኖች በበኩላቸው በስልጠና ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት ተግባራዊ በማድረግ የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።


በስልጠና ቆይታቸው የላቀ አፈጻጸም ያሳዩ መኮንኖች የዋንጫ ሽልማት ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተበርክቶላቸዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም