የኮሙኒኬሽን ሥራዎች በሕዝቦች መካከል መልካም መስተጋብር በመፍጠርና ችግሮችን በመፍታት ረገድ ጉልህ ሚና አላቸው -ዶክተር ለገሰ ቱሉ

አዲስ አበባ መጋቢት 30/2015 (ኢዜአ)፦የኮሙኒኬሽን ሥራዎች በሕዝቦች መካከል መልካም መስተጋብር በመፍጠርና ችግሮችን በመፍታት ረገድ ጉልህ ሚና እንዳላቸው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ገለጹ።

“ውጤታማ ተግባቦት ለኢትዮጵያ ልዕልና” በሚል ርዕስ ለፌዴራል ተቋማት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች፣ ለክልሎችና ከተማ መሥተዳድሮች የኮሙኒኬሽን ኃላፊዎች እንዲሁም ለመገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎች ሥልጠና እየተሰጠ ነው።


 

በሥልጠና መርሐ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ የኮሙኒኬሽን ሥራዎች በሕዝቦች መካከል መልካም መስተጋብር በመፍጠርና ችግሮችን በመፍታት ረገድ ጉልህ ሚና እንዳላቸው አስገንዝበዋል።

እንደሀገር ከተጀመረው የለውጥ ጉዞ፣ አዲስ ተላምዶና አቅጣጫ ጋር የሚጣጣም የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራ እንደሚያስፈልግም ሚኒስትሩ  አሳስበዋል።

የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ መልካም መስተጋብር ለመፍጠር፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፍላጎቶችን ለማሳካት ጉልህ ሚና የሚጫወት የተግባቦት ዘዴ በመሆኑ በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በአጀንዳ ቀረጻ ላይ የሚታዩ መሰረታዊ ችግሮችን መፍታት እና ለምን አይነት ጉዳይ ምን አይነት የኮሙኒኬሽን አካሄድ ልንከተል ይገባናል ብሎ ማሰብ እንደሚገባም ሚኒስትሩ በንግግራቸው ጠቁመዋል። 

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በጋራ ያዘጋጁት ይሄው ስልጠና ለአራት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን ከ200 በላይ የኮሙኒኬሽን አመራርና ባለሙያዎችም ተሳታፊ ሆነዋል።

በመርሃ ግብሩ የመደመር ትርክት እና የኢትዮጵያ ብልፅግና ጉዞ፣የሕዝብ ግንኙነት መሰረቶች እና አጀንዳ ቀረጻ ፤ የቀውስ ጊዜ ኮሙኒኬሽን፣ የሚዲያ አስተዳደርና ለሕዝብ የሚደረጉ ንግግሮች በሚሉ ርዕሶች ላይ ስልጠናና ውይይት ይካሄዳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም