የነዳጅ ግብይት በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርዓት መታገዙ ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት እንድናገኝ አስችሎናል -አሽከርካሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የነዳጅ ግብይት በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርዓት መታገዙ ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት እንድናገኝ አስችሎናል -አሽከርካሪዎች
አዲስ አበባ መጋቢት 30/2015 (ኢዜአ)፦ "በአዲስ አበባ በሙከራ ደረጃ የተጀመረው የኤሌክትሮኒክስ የነዳጅ የክፍያ ስርዓት ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት እንድናገኝ አስችሎናል" ሲሉ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ አሽከርካሪዎች ተናገሩ።
የነዳጅ ማደያ ባለቤቶች በበኩላቸው ስርዓቱ የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን በማስቀረት ሕገ-ወጥነትን መከላከል እንደያስችል ገልጸዋል።
ኢዜአ በአዲስ አበባ የተጀመረው የዲጂታል የነዳጅ ግብይትን አስመልክቶ በተለያዩ ማደያዎች በመዘዋወር የግብይት ሂደቱን ቃኝቷል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አሽከርካሪዎች፤ የዲጂታል የክፍያ ሥርዓቱ ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ከማስቻሉ ባሻገር ''ቀልጣፋ የግብይት ስርዓት እንዲፈጠር አድርጓል'' ይላሉ።
አሰራሩ ሕገ-ወጥ የነዳጅ ግብይትን በማስቀረትና ስርዓት አክብረው የሚገለገሉ ተጠቃሚዎች ነዳጅ በበቂ ሁኔታ ተደራሽ እንዲሆን ማድረጉን ገልጸዋል።
ተጠቃሚው ነዳጅ ለመግዛት በሚያደርገው የገንዘብ ዝውውርም ለዘረፋ እንዳይጋለጥ ከማድረጉ በተጨማሪ ጊዜ ቆጣቢ መሆኑንም አንስተዋል።
በተጨማሪም የነዳጅ ግብይቱን ከሕገ-ወጥነት የፀዳ በማድረግ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ያግዛል ሲሉ ተናገሩት ደግሞ የነዳጅ ማደያ ባለቤቶች ናቸው።
የተጀመረው የዲጂታል የነዳጅ ግብይት የነዳጅ ብክነትን በማስቀረት ረገድም አስተዋጽኦ የሚያበረክት ና ጥሬ ገንዘብ ይዞ የመንቀሳቀስ ሁኔታ እንደሚያስቀር ገልጸዋል።
የነዳጅ ድጎማና ሪፎርም አስተባባሪና የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አብዱልበር ሸምሱ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከሚካሄዱባቸው ዘርፎች መካከል የነዳጅ ግብይት ትልቁን ድርሻ ይይዛል።
ቀደም ሲል የነዳጅ ግብይቱ ወጥነት ያለው አሰራርን ያልተከተለ በመሆኑ የአጠቃቀምና የስርጭት ሂደቱ ክፍተቶች እንደነበሩበት አንስተዋል።
ከዚህ ባሻገር አሰራሩ ፍትሐዊ ተደራሽነት ላይም ጫና ማሳደሩን አመልክተው፤ ከፍተኛ የነዳጅ ሃብት ብክነት እንዲፈጠር ማድረጉንና በዚህም ሳቢያ ዘርፉ ለሕገ-ወጥ ተግባራት ተጋላጭ ሆኗል ብለዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚዎች ተግባራዊ ሲደረግ መቆየቱን ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያመለከቱት።
በቀጣይ ከሚያዚያ 16 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ሁሉም ተሽከርካሪ በዲጂታል የክፍያ ስርዓት እንዲጠቀሙ እንደሚደረግና ከግንቦት 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ አሰራሩ በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል።
ዲጂታል የነዳጅ ግብይቱ በአሁኑ ወቅት በቴሌ ብር እየተከናወነ ሲሆን፤ በቀጣይም መስፈርቱን የሚያሟሉ የፋይናንስ ተቋማት አገልግሎቱን መስጠት የሚችሉበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑንም አክለዋል።