ቀጥታ፡

በጨርቃጨርቅ ዘርፍ የሙያተኞችን አቅም ለማሳደግና የሥራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል ሥምምነት ተፈረመ

 አዲስ አበባ መጋቢት 30/2015 (ኢዜአ)የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በጨርቃጨርቅ ዘርፍ የሙያተኞችን አቅም ለማሳደግና የሥራ እድል መፍጠር የሚያስችል ሥምምነት ኦሬንት ኢንተርናሽናል ሆልዲንግ ከተሰኘ የቻይና ኩባንያ ጋር ተፈራረመ።   

ሥምምነቱን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ተሻለ በርቻና በኢትዮጵያ የኦሬንት ኢንተርናሽናል ሆልዲንግ ተወካይ ሹዌ ጂ ፌንግ ፈርመውታል። 

ሥምምነቱ በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራትና በኩባንያው የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑም ተጠቁሟል።

ሚንስትር ዴኤታው በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት የግሉ ሴክተር ለዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው። 

የአምራች ኃይሉን አቅም ማጎልበት ላይም እንዲሁ።

ይህ ሥምምነት አገሪቱ በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ የጀመረችውን የልማት እንቅስቃሴ ለማሳደግ የሚያግዝ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።

በቅርቡም በጨርቃ ጨርቅ የተሰማሩ 100 ዜጎች ወደ ቻይና ሄደው እንደሚሰለጥኑም ገልጸዋል።

የኦሬንት ኢንተርናሽናል ሆልዲንግ ሊቀመንበር ቶንግ ጂ ሼንግ በበኩላቸው፤ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ብቁና የሰለጠነ ሙያተኛና ቴክኖሎጂን የሚጠይቅ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህንንም በኢትዮጵያ ለማፍራት ድርጅታቸው አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በኩባንያው ሥር የሚገኘው ሻንግቴክስ የጨርቃጨርቅ አምራች በዘርፉ የካበተ ልምድ እንዳለው የጠቀሱት ሊቀመንበሩ፤ በቀጣይም  በኢትዮጵያ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናደርጋለን ነው ያሉት፡፡

በቀጣይም 100 የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ወደ ቻይና ሄደው በዘርፉ የሚሰለጥኑበት ሁኔታ እንደሚመቻች አስረድተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም