ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ የሚያሻግር ትውልድ ማፍራት ላይ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል --ዶክተር ነገሪ ሌንጮ - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ የሚያሻግር ትውልድ ማፍራት ላይ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል --ዶክተር ነገሪ ሌንጮ
አዲስ አበባ መጋቢት 30 /2015(ኢዜአ)፡- ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ የሚያሻግር ትውልድ ማፍራት ላይ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ገለጹ።
የዩኒቨርሲቲዎች የራስ ገዝ አስተዳደር ረቂቅ አዋጅን በሚመለከት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንቶች ጋር የግብአት ማሰባሰቢያ የውይይት መድረክ እያካሄዱ ነው።
በመድረኩ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የሰው ሀብት ልማት፣ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ፣ የምክር ቤት አባላት፣ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የምክክር መድረክ የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሐና እና ሌሎች የዩኒቨርሲቲ ተወካዮች ተገኝተዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ሀገርን በመገንባት ሂደት ምሁራን የመሪነቱን ሚና ሊወጡ ይገባል።
ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ የሚያሻግር ትውልድ ማፍራት ላይ በትኩረት እንዲሰሩም አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ ያሉባትን ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች ተቋቁማ ለማለፍ ሁሉን አቀፍ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ይህን ለማሳካት ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት፣ ሀገርን የሚጠቅም ምርምር ለማካሄድም የትምህርት ተቋማት ጥራትን መሰረት ያደረገ አደረጃጀትን መከተል እንዳለባቸው አንስተዋል።
የዩኒቨርሲቲዎች ራስገዝ ረቂቅ አዋጅ የተዘጋጀውም ለዚሁ ዓላማ ነው ብለዋል።
የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የምክክር መድረክ የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሐና በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ማድረግ ያስፈለገው ተቋማዊ እና አስተዳደራዊ ነጻነት እንዲኖራቸው መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን ላይ ያለው አሰራር በሲቪል ሰርቪስ በወጡ መመሪያዎች መሆኑ ለዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት እና ተቋማዊ ነጻነት ምቹ አለመሆኑን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር፣ በትምህርት፣ በማህበረሰብ ለውጥ ልቀው እንዲወጡ የአስተዳደር ነጻነት ዋነኛው መሆኑን አመላክተዋል።