ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም በአንድነትና በጽናት መጠበቅ የሚችሉ ሕዝቦች ናቸው - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ መጋቢት 29/2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም በአንድነትና በጽናት መጠበቅ የሚችሉ ሕዝቦች መሆናቸውን የትናንት ታሪክና የቅርብ ጊዜ ሁኔታ ሁነኛ ማሳያ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ።

መገናኛ ብዙኃንና የኮሙዩኒኬሽን ተቋማትም የሰላምና ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን በማጎልበት ለአገር ብሔራዊ ጥቅም መከበር በኃላፊነት መንፈስ ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር "መገናኛ ብዙኃን ለብሔራዊ ጥቅም" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

በምክክር መድረኩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ተቋማት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ኢዜአ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበርን በሚመለከት አጀንዳ ማዘጋጀቱ ምስጋና ይገባል ብለዋል። 

ኢትዮጵያውያን በተሰማራንበት የሥራ መስክ ሁሉ የሕዝቦችን ጥቅም በማስቀደም የአገርን ብሔራዊ ክብርና ጥቅም ማስቀጠል ይኖርብናል ብለዋል።

ኢትዮጵውያን የአገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም በአንድነትና በጽናት መጠበቅ የሚችሉ ህዝቦች መሆናቸውን የትናንት ታሪክና የቅርብ ጊዜ ሁኔታ ሁነኛ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

የአገርን ልዕልና ማስጠበቅ ከትውልድ ትውልድ፣ ከመንግሥት መንግሥት ሲሸጋገር የመጣ መለያ ባህሪ እንደሆነም ተናግረዋል።

የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ተቋማት የአገርን ብሔራዊ ጥቅም ለድርድር ባለማቅረብ ሰላምና ዴሞክራሲ ግንባታን ማጠናከር የኢትዮጵያ የህልውና ጉዳዮች መሆኑን ተገንዝበው በኃላፊነት መንፈስ መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

መንግሥት ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አስጠብቆ ማስቀጠል የሚያስችል ውጤታማ የለውጥ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን አንስተዋል።

በሕዝቦች ጽናት ፈተናን መሻገር የሚያስችል ስኬት መመዝገቡን ጠቁመው ኢትዮጵያውያንም በወንድማማችነት መንፈስ ብልጽግናቸውን ማረጋገጥ እንደሚችሉ መገንዘብ ተችሏል ብለዋል።

አገር እያጋጠማት ያለውን ፈተና በማለፍ የተመዘገቡ ስኬቶችንና ተስፋ ሰጪ ምልክቶችን እጅ ለእጅ ተያይዞ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

በሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ የተሰማሩ አካላትም በዕለት ተዕለት ተግባራቸው በሚያከናውኗቸው ሥራዎች የአገርን ብሔራዊ ጥቅም በማስቀደም ለሰላምና ዴሞክራሲ ግንባታ ልዩ ሚና መጫወት እንዳለባቸው አሳስበዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ ኢዜአ እድሜ ጠገብ አንጋፋ ከሆኑ የኢትዮጵያ የሚዲያ ተቋማት አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም ተቋሙ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መከበር ካለው ሚና አንፃር በማቋቋሚያ አዋጅ እንደገና ተደራጅቶ የዜና አገልግሎት ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢዜአ 80ኛ ዓመቱን ሲያከብር የአገር ብሔራዊ መግባባትን በማጠናከር የኢትዮጵያን ድምጽና እውነት ማሳወቅ እንዳለበት አቅጣጫ መስጠታቸውን አስታውሰዋል።

የተሰጠውን ተልዕኮ ለማከናወን ከሚሰራቸው ተግባራት ጎን ለጎንም በ2022 ዓ.ም በአፍሪካ ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ለመሆን እየተጋ እንደሚገኝም አንስተዋል።

በዚህም በእንግሊዝኛና አረብኛ ቋንቋዎች ከሚሰራቸው ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎች በተጨማሪ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ሥራ እንደጀመረ ጠቁመዋል።

በቅርቡም በማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ በሚገኘው የሚዲያ ኮምፕሌክስ በእንግሊዝኛና አረብኛ ቋንቋዎች የቴሌቪዥን የሙከራ ሥርጭት ይጀምራል ብለዋል።

በአዲስ ዓመት መደበኛ ሥርጭት እንደሚጀምር ጠቁመው ኢትዮጵያ በራሷ ቀለም የአፍሪካ ድምጽ በመሆን "ኢትዮጵያን በ2022 የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት" ለማድረግ የተያዘውን ውጥን ለማሳካት አስተዋዕኦ ይኖረዋል ብለዋል።


 

ኢትዮጵውያን አገራቸውን የባለቤትነት ስሜት ማስቀጠል ይኖርባቸዋል ያሉት ደግሞ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሃመድ እድሪስ ናቸው።

የአገርን ብሔራዊ ጥቅም አስጠብቆ ለማስቀጠል ሁሉም ዜጋ በታላቅ የኃላፊነት መንፈስ በመቀራረብ እና በአንድነት መሥራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ የተሰማሩ አካላት የአገርን አንድነት ማስጠበቅ የሚያስችሉ ሚዛናዊ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ የአገርን ከፍታ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

በምክክር መድረኩ የመገናኛ ብዙሃን ለአገር ብሔራዊ ጥቅም መከበር፣ ለዴሞክራሲና ሰላም ግንባታ ያላቸውን ሚና በሚመለከት የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም