ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል የሓዋላ አገልግሎትን ለማቀላጣፍ የሚያስችለውን ሥምምነት አደረገ 

አዲስ አበባ  መጋቢት 29/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ "ካሽ ጎ" የተሰኘ የዲጂታል መተግበሪያ በመጠቀም የውጭ የሓዋላ አገልግሎትን ለማቀላጠፍ የሚያስችለውን ሥምምነት "ጎልደን ኮፊ ሮስተሪ"  ከተባለ ተቋም ጋር ሥምምነት ተፈራረመ።  

ሥምምነቱን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዘዳንት አቶ አቤ ሳኖ እና  የ"ጎልደን ኮፊ ሮስተሪ" ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሃላፊ አቶ ቴወድሮስ ሺፈራው ፈርመውታል። 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዘዳንት አቶ አቤ ሳኖ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ባንኩ ዲጂታል መተግበሪያዎችን በመጠቀም ለደንበኞች ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ ነው። 

ባንኩ ዲጅታል መተግበሪያዎችን በመጠቀም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 549 ግብይቶችን በማድረግ ከ2 ነጥብ 1 ትርሊየን ብር በላይ አንቀሳቅሷል ብለዋል። 

በዛሬው ዕለት የተደረሰው ሥምምነት የክፍያ ሥርዓትን ለማዘመንና የውጭ ሓዋላ አገልግሎትን ለማቀላጠፍ የሚረዳ መሆኑን ጠቁመዋል። 

ባንኩ በቅርቡ በራሱ "ኢትዮ-ዳይሬክት" የተሰኘ የዲጂታል ሓዋላ መላኪያ  መተግበሪያ ማበልጸጉን ገልጸው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መተግበሪያውን በመጠቀም የውጭ ምንዛሬ እንዲልኩ ማስቻሉን ገልጸዋል። 

በዛሬው ሥምምነት ጎልደን ኮፊ ሮስተሪ ያበለጸገውን "ካሽ-ጎ" መተግበሪያ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውን ከጎግል ወይም አፕል ስቶር በማውረድ የክፍያ ካርዳቸውን በመጠቀም ገንዘብ ለቤተሰቦቻቸው መላክ ያስችላቸዋል ነው ያሉት። 

መተግበሪያው ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ፋይዳው የጎላ መሆኑን አንስተው አገልግሎቱም ቀላል፣ ምቹና ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆኑም ነው የጠቀሱት።

ደንበኞች ዓለም አቀፍ ካርዶችን የማስተርና ቪዛ ካርዶችን በመጠቀም ያለምንም የአገልግሎት ክፍያ ከዘጠኝ አገራት ዶላር ወደ አገር ቤት መላክ ማስቻሉ "ካሽ-ጎ"ን ለየት ያደርገዋል ብለዋል። 


 

ጎልደን ኮፊ ሮስተሪ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሃላፊ አቶ ቴወድሮስ ሺፈራው በበኩላቸው  መተግበሪያው የበለጸገው በአገር ውስጥ ባለሙያዎች ነው ብለዋል። 

በአንድ ወር ጊዜ ውስጥም ከአምስት እስከ 1 ሺህ ዶላር የውጨ ምንዛሬ ከካናዳ፣ ከአሜሪካ፣ ከእስራኤል፣ ከሳውዲ፣ ከተባበሩት አረብ ኢምሬት፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከእንግሊዝ፣ ከስዊድንና ከጣሊያን መላክ ያስችላቸዋል ነው ያሉት።     

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም