ለቴክኖሎጂ ሽግግር መጎልበት የሚረዱ የምርምር ስራዎች እያካሄድኩ ነው - ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ - ኢዜአ አማርኛ
ለቴክኖሎጂ ሽግግር መጎልበት የሚረዱ የምርምር ስራዎች እያካሄድኩ ነው - ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ

ሐዋሳ መጋቢት 29/2015 (ኢዜአ) ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የኢንዱስትሪ ትስስርን በማጠናከር ለቴክኖሎጂ ሽግግር መጎልበት የሚረዱ የምርምር ስራዎች እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ።
የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተሳተፉበት 5ኛው ዓመታዊ የቴክኖሎጂና ኢንጅነሪንግ የምርምር ኮንፍረንስ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው፡፡
የዩኒቨርሲቲው አካደሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ኢንጅነር ፍስሃ ጌታቸው እንደገለጹት በመድረኩ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በቴክኖሎጂና ኢንጂነሪንግ ዘርፍ የተሰሩ 16 የምርምር ስራዎች ይቀርባሉ፡፡
የምርምር ስራዎቹ ችግር ፈቺ የሆኑና በኢንዱስትሪው ዘርፍ ጉልህ ሚና የሚጫወቱ መሆናቸውን ጠቁመው በአጭር ጊዜ ውስጥ በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ እንደሚታተሙ አመላክተዋል፡፡
ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስርን በማጠናከር የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማጎልበት የሚያስችሉ የምርምር ስራዎችን እያካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት ከሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጋር በጋራ ያከናወናቸው የምርምር ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸው "ጅምር ቢሆኑም ውጤታማ ናቸው" ብለዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የፓርኩን መከፈት ተከትሎ በጨርቃ ጨርቅና አልበሳት ላይ አዲስ ትምህርት ክፍል ከፍቶ ተማሪዎችን ማስተማር መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
ችግር ፈቺ የሆኑ የምርምር ስራዎች የችግሩን ባለቤቶች የምርምሩ አካል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል" ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ "ኢንዱስትሪዎችም የኮንፍረንሱ ተሳታፊ የሆኑት ለዚሁ ነው" ሲሉ አክለዋል፡፡
የምርምር ኮንፍራንሱ ተመራማሪዎችን፣ ኢንደስትሪዎችንና ዩኒቨርሲቲዎችን በማገናኘት በዘርፉ ለሚከናወነው የቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶክተር ኢንጂነር ፋሲካ ቤተ በበኩላቸው የዘንድሮው ዓመታዊ የምርምር ኮንፍረንስ ለሁለተኛ ጊዜ ከሃዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡
አስር የሚደርሱ ዩኒቨርሲቲዎች በተሳተፉበት የምርምር ኮንፍረንስ በቴክኖሊጂና ኢንጅነሪንግ ዘርፍ የተሰሩ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን ከማቅረብ ባለፈ ዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስሩን ማጠናከር ያለው ጠቀሜታ እንደሚመላከትበት ተናግረዋል፡፡
የምርምር ስራዎቹ በኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ሊፈቱ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን መፍጠር የሚያስችሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
"እንደ ሃገር ለማምጣት የታሰበውን ሁለንተናዊ ለውጥ ለማሳካትና የህብረተሰቡን ህይወት ለመቀየር የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስርን ማጠናከርና በጋራ መስራት ይገባል" ብለዋል፡፡
ለተግባራዊነቱም ዩኒቨርሲቲው ከሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጋር በጀመራቸው በርካታ የምርምር ስራዎች ወደ ትግበራ የገቡና በሂደት ላይ ያሉ መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ከዩኒቨርሲቲው ጋር የስምምነት ሰነድ በመፈራረም የተጀመሩ የምርምር ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ማቲዎስ አሸናፊ ናቸው፡፡
በፓርኩ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የተግባር ልምምድ እንደሚያደርጉና በፓርኩ ለሚያጋጥሙ የተለያዩ ችግሮችም በምርምር የታገዘ ስራ ከዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች ጋር እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በዚህም አካባቢን በማይበክል መልኩ ከፓርኩ የሚወገደውን ፍሳሽ መልሶ በመጠቀም ለግንባታ ዘርፉ የሚያገልገሉ የተለያዩ ግብዓቶችን ማምረት መጀመራቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በፓርኩ የሚመረቱ ምርቶች ዓለም አቀፍ ገበያ ላይ የሚቀርቡ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ያለውን ትስስር ማጠናከር ተወዳዳሪ ለመሆንና የቴክኖለጂ ሽግግር ለማድረግ እንደሚያግዝ ዋና ስራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።
በዓመታዊ የምርምር ኮንፍረንሱ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከቀረቡ የምርምር ስራዎች በተጨማሪ ኢንዱስትሪዎችም ልምዳቸውን አቅርበው ውይይት እየተደረገ ይገኛል፡፡