በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስና ሲዳማ ቡና ነጥብ ተጋርተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስና ሲዳማ ቡና ነጥብ ተጋርተዋል
አዲስ አበባ መጋቢት 29/2015(ኢዜአ)፦ በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ18ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስና ሲዳማ ቡና አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተለያይተዋል።
በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ጋናዊው የፊት መስመር ተሰላፊ ፍሊፕ አጃህ ጨዋታው በተጀመረ በሶስተኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ ሲዳማ ቡናን መሪ ማድረግ ችሎ ነበር።
ይሁንና ከእረፍት መልስ ተቀይሮ የገባው ዳግማዊ አርአያ በ83ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ ቅዱስ ጊዮርጊስን አቻ አድርጋለች።
ውጤቱንም ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን ወደ 39 ከፍ በማድረግ ከተከታዮቹ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ስድስት አስፍቷል።
በአንጻሩ ሲዳማ ቡና ነጥቡን ወደ 20 ከፍ በማድረግ በነበረበት 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በ18ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ መርሐ-ግብር አርባ ምንጭ ከተማ ከመቻል ከምሽቱ 12 ሰአት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።