በኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችን ለማስቀጠል የአጋር አካላት ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት - ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችን ለማስቀጠል የአጋር አካላት ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት - ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ
አዲስ አበባ መጋቢት 29/2015(ኢዜአ) በኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችን ለማስቀጠል የአጋር አካላት ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ ገለጹ።
የጤና ሚኒስቴር ከዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ጋር በመተባበር ዓለም አቀፍ የጤና ቀንና ድርጅቱ የተመሰረተበትን 75ኛ ዓመት አክብሯል።
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ባለፉት ዓመታት በጤናው ዘርፍ አመርቂ ውጤቶች ተመዝገበዋል።
ለአብነትም የእናቶችና የሕጻናት ሞትን ለመቀነስ በተሰራ ሥራ ለአፍሪካ አርአያ የሚሆን ተግባር መከናወኑን አስታውሰዋል።
በተጨማሪም በኤች አይቪ ኤድስ፣ በወባና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች የሚከሰተውን ሞት በመቀነስ ረገድ ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን ጠቅሰዋል።
በቅርቡም ኮቪድ 19ኝ ጨምሮ የተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች በአገሪቱ የጤና አገልግሎት አሰጣጥና ተደራሽነት ላይ ዓሉታዊ ተጽዕኖ ቢያሳድሩም ከአጋር አካላት ጋር በመሆን በተሰራው ሥራ አበረታች ውጤት መገኘቱን አስረድተዋል።
በመሆኑም በጤናው ዘርፍ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችን ለማስቀጠል ብሎም የዘርፉ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ኖህላንኸላ ዲላሚኒ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የሴቶችን የሕጻናትን የጨቅላ ሕጻናትን ሞት በመቀነስ ረገድ ወሳኝ ሥራ መሰራቱንና በዚህም ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል።
በአገሪቱ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በመከላከል እንዲሁም የዜጎችን ሞት ለመቀነስ የተሰራውን ሥራ በአድናቆት እንደሚመለከቱት ገልጸዋል።
አያይዘውም የስኳር፣ የደም ግፊት፣ የልብ ህመምና የአንጎል ውስጥ ደም መፍሰስ ወይም ስትሮክን የመሳሰሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስርጭት እየጨመረ በመምጣቱ ይህንን ለመቀነስ በትብብር መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
አገሪቱ የጤናውን ዘርፍ በማሻሻል አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ እያከናወነች ያለው ተግባር ለውጥ እንዲያመጣ የዓለም ጤና ድርጅት አጋርነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።