ቀጥታ፡

ለድርቅ ተጎጂዎች እየተደረገ ያለውን የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ከማጠናከር ጎን ለጎን የዘላቂ መፍትሔ ፍኖተ ካርታ ይዘጋጃል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ መጋቢት 29/2015(ኢዜአ)፡- ለድርቅ ተጎጂዎች እየተደረገ ያለውን የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ከማጠናከር ጎን ለጎን የዘላቂ መፍትሔ ፍኖተ ካርታ እንደሚዘጋጅ ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት አመራር ምክር ቤት ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት አመራር ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የድርቅ አደጋዎች ምላሽ የአራት ወራት እቅድና አፈጻጸም ላይ ተወያይቷል።  


 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በድርቅ ተጎጂ ለሆነው ማኅበረሰብ አስቸኳይ ምላሽ ለመስጠት እየተደረገ ያለው ርብርብ ውጤት እያመጣ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ምክር ቤቱ ባለፈው አንድ ወር ያከናወነው የድርቅ አደጋ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ መልካም መሆኑን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት በድርቅ ተጎጂ በነበሩ አካባቢዎች እየዘነበ ያለውን ዝናብ በአግባቡ ለመጠቀምና የጎርፍ አደጋ ጉዳት እንዳያደርስ መረባረብ እንደሚገባም አንስተዋል።


 

በጤና፣ በውሃ፣ በግብርናና በመስኖና ቆላማ ተቋማት የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በተለይም የእርሻ መሣሪያዎች አቅርቦትና የመኖ ዝግጅት ትኩረት ሊሠጣቸው ይገባል ነው ያሉት።

በቀጣይም መረጃ ላይ የተመሠረተ የተረጂዎችን ቁጥር በመለየት ምላሽ የመሥጠት ሥራን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

ድርቅና ግጭት ያስከተሉትን ችግር መሻገር የሚያስችል አገራዊ አቅም መኖሩን ገልጸው ሰብዓዊ ድጋፎችም ለተረጂዎች በቀጥታ መድረሳቸውን ማረጋገጥ የሁሉም የቤት ሥራ ነው ብለዋል።

መጪውን ጊዜ በአስተማማኝ ሁኔታ ለመሻገር ድርቅ፣ ጎርፍና ግጭት ያመጧቸውን ፈተናዎች በመቋቋም ዕድሎችን በአግባቡ መጠቀም አለብን ሲሉም ገልጸዋል።

ለዚህም ከፌዴራል እስከ ክልል ሁሉም ተቋማትና አጋር አካላት ቅንጅታዊ አሰራራቸውን እንዲያጠናክሩ አሳስበው ምክር ቤቱም አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።


 

በቀጣይም ለሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ዘላቂ መፍትሔ ሊቀመጥ እንደሚገባ ገልጸው በተለይም የቆላማ አካባቢ ልማት በመካከለኛ ዘመን እቅድ ውስጥ በአግባቡ መካተቱን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለአስቸኳይ ጊዜ የአደጋ ምላሽ መረባረብና የዘላቂ ጊዜ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀትም የቀጣይ ሥራችን ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።


 

የብሔራዊ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ዶክተር ሺፈራው ተክለማርያም በበኩላቸው ከመጋቢት ጀምሮ እየተተገበረ ባለው የድርቅ አደጋ ምላሽ እቅድ ሰፊ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።  

በዚህም በኦሮሚያ፣ በሶማሌ፣ በደቡብና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የድርቅ ተጎጂ የሆኑ ከ11 ሚሊዮን በላይ ዜጎች መኖራቸውን አንስተው የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ለሚሹ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ፈጣን ምላሽ መስጠትን ጨምሮ በየደረጃው አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተለይም ድርቁና ሰሞኑን እየጣለ በሚገኘው ዝናብ በፈጠረው ጎርፍ ምክንያት የሰው ህይወት እንዳይጎዳ በተቋማዊ ቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል። 


 

የሴክተር መሥሪያ ቤት ኃላፊዎችም በጤና፣ በግብርና፣ በመስኖ፣ በውሃ ዙሪያ በትኩረት እየሠራን ነው ብለዋል።

የበሽታ ሥጋት ክትትል፣ ህክምና፣ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮና ዘላቂ የቆላማ አካባቢ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸው ተነስቷል።

የእንስሳት በሽታ እንዳይከሰት መከላከልና በቂ መኖ አቅርቦት ላይም እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።   

በድርቅ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት በመካከለኛ ዘመን እቅድ ውስጥ አካትቶ እንዲሠራ አቅጣጫ ተቀምጧል።

የፌዴራልና የክልል አስቸኳይ ጊዜ የአደጋ ምላሽ ማስተባበሪያዎች በተቀናጀ መልኩ እየሠሩ ሲሆን የጎርፍ አደጋ መከላከል ግብረ-ኃይል መቋቋሙ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም