ቀጥታ፡

የጸጥታ አካላት የደንብ ልብስ በሀገር ውስጥ በማምረት 60 ሚሊዮን ዶላር ማዳን ተችሏል- አቶ መላኩ አለበል

አዲስ አበባ መጋቢት 29/2015 (ኢዜአ)፦ የጸጥታ አካላት የደንብ ልብስን በሀገር ውስጥ በማምረት 60 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በአገር አቀፍ ደረጃ የጸጥታ ተቋማት የአልባሳት አቅርቦት አፈጻጸም ላይ ከፌዴራልና ከክልል የጸጥታ አካላትና ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።


 

አቶ መላኩ አለበል በ ‘ኢትዮጵያ ታምርት’ አገራዊ ንቅናቄ ከውጪ ይገቡ የነበሩ ያለቀላቸው ምርቶችን ጥራታቸውን በጠበቁ የአገር ውስጥ ምርቶች በመተካት የእሴት ጭማሬውን 62 በመቶ ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ የጸጥታ ተቋማት የደንብ ልብስ በአገር ውስጥ የመተካት ሂደት ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑና በእስካሁኑ ሂደት ከ18ሺህ በላይ የዜጎችን የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል፡፡


 

የጸጥታ አካላት የደንብ ልብስ በአገር ውስጥ በማምረት ሂደት ላይ 18 ፋብሪካዎች የተሳተፉ መሆኑን ገልጸው በዚህም 60 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉን አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አንዱ አካል የሆነው የጸጥታ አካላት የደንብ ልብስ በአገር ውስጥ ማምረትና የውስጥ ፍላጎትን የመሸፈን ጉዳይ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በአገር ኢኮኖሚ ውስጥ ጉልህ ድርሻ እየተጫወቱ ያሉትን አምራች ኢንዱስትሪዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር በማቀናጀት በላቀ የአመራር ብቃት ውስጣዊ ጥንካሬዎችን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም