በራያ ቆቦ ወረዳ ጉዳት ደርሶበት የነበረው የመስኖ አውታር በመልሶ ማደራጀት ወደ ልማት መግባቱ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በራያ ቆቦ ወረዳ ጉዳት ደርሶበት የነበረው የመስኖ አውታር በመልሶ ማደራጀት ወደ ልማት መግባቱ ተገለጸ
ወልዲያ መጋቢት 29/2015(ኢዜአ)፦ በሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ በጦርነቱ ጉዳት ደርሶበት የነበረውን የመስኖ አውታር መልሶ በማደራጀት 1ሺህ 536 ሄክታር መሬት ማልማት መቻሉን የቆቦ ጊራና ሸለቆ ልማት ፕሮግራም ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሞላ መለሰ ለኢዜአ እንደገለጹት የመስኖ አውታር ዝርጋታው ከግጭቱ በፊት 2ሺህ 885 ሄክታር መሬት ያለማ ነበር።
በነበረው ጦርነት ለመስኖ ሥራው አጋዥ የሆኑ ትራንስፎርመርና ሌሎች የኤሌክትሪክ አገልግሎቶች ለጉዳት ተጋልጠው የመስኖ አውታሩ ለሁለት ዓመት ተስተጓጉሎ መቆየቱን ገልጸዋል።
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በክልሉ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ቢሮ እንዲሁም በየደረጃው ካሉ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ተቋማት ጋር በመተባበር በከፊል ሥራ ለማስጀመር መቻሉን ገልጸዋል።
የመስኖ አውታር ዝርጋታው መልሶ ወደ ሥራ እንዲገባ የክልሉ መንግስት 58 ሚሊዮን ብር መመደቡንም አቶ ሞላ ተናግረዋል።
በተቀናጀ መንገድ በተሰራው ሥራ በኤሌክትሪክና በፀሐይ ኃይል የሚሰራ ሶላር በመጠቀም 1ሺህ 536 ሄክታር መሬት መልሶ እንዲለማ መደረጉን አቶ ሞላ አብራርተዋል።
ከለማው መሬት ውስጥ 109 ሄክታሩ በክላስተር ስንዴ ሰብል የለማ መሆኑንም ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት እየጣለ ያለውን የበልግ ዝናብ በመጠቀምም 864 ሄክታር መሬት በተጨማሪነት እንዲለማ መደረጉን ነው የገለጹት።
በዚሁ የመስኖ ልማት ከ1ሺህ 800 በላይ አባወራና እማውራዎች ተሳታፊ መሆናቸውንም አመልክተዋል።
የመስኖ አውታሩን በመጠቀም ከሚለማው ስንዴ በተጨማሪ ሽንኩርት፣ ጥቅል ጎመን፣ ሃብ ሃብና ሌሎች አትክልትና ፍራፍሬዎችን የማልማት ሥራ እየተሰራ ነው።
የቆቦ ጊራና ሸለቆ ልማት ፕሮግራም የማልማት አቅሙን ሙሉ ለሙሉ ለመጠቀም ቀሪ መሰረተ ልማቶችን የማሟላት ሥራዎች በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በራያ ቆቦ ወረዳ የጎለሻ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ኑሩ ፈረጃ በበኩላቸው በተዘረጋው የመስኖ አውታር ለረጅም ጊዜ ሲጠቀሙ እንደነበር አስታውሰዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በአካባቢያቸው ተፈጥሮ በነበረ የጸጥታ ችግር የመስኖ አውታሩ አገልግሎት መስጠት አቋርጦ እንደነበር ገልጸዋል።
ይሁንና በአሁኑ ወቅት የመስኖ አውታሩ ዳግም ሥራ በመጀመሩ አንድ ሄክታር መሬት ስንዴ በመስኖ እያለሙ መሆኑን ተናግረዋል።
በራያ ቆቦ ወረዳ የአዲስ ቅኝ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አገርነሽ ካሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በከርሰ ምድር መስኖ 1 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ቲማቲም፣ ሽንኩርት እና ስንዴ በማልማት ላይ መሆናቸውን እያለሙ መሆኑን ገልጸዋል።
ለልማቱም መንግስት ምርጥ ዘር በነፃ እያቀረበላቸው መሆኑንና የአፈር ማዳበሪያም በቅናሽ ዋጋ ገዝተው መጠቀማቸውንም አርሶ አደሮቹ ገልጸዋል።
የቆቦ ጊራና ሸለቆ ልማት ፕሮግራም ከቆቦ እስከ ጊራና ሦስት ወረዳዎችን በከርሰና ገጸ-ምድር ውሃ አርሶ አደሩን የመስኖ ተጠቃሚ በማድረግ ምርታማነቱን ለማሳደግ ታስቦ የተዘረጋ መሆኑ ታውቋል።