የክልል ልዩ ኃይል መልሶ ማደራጀት ተልዕኮው ጠንካራ የተማከለ ሰራዊት ለመገንባት ያለመ ነው - የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
የክልል ልዩ ኃይል መልሶ ማደራጀት ተልዕኮው ጠንካራ የተማከለ ሰራዊት ለመገንባት ያለመ ነው - የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ መጋቢት 29/2015 (ኢዜአ) የክልል ልዩ ኃይል መልሶ ማደራጀት ተልዕኮው ከአገር ውስጥና ከውጭ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች የሚመክት ጠንካራ የተማከለ ሰራዊት ለመገንባት ያለመ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮችን አስመልክተው ዛሬ በሰጡት መግለጫ የልዩ ኃይል መልሶ ማደራጀት ሥራው መንግስት በፀጥታ መዋቅሩ ላይ የጀመረው ሪፎርም አካል መሆኑን ጠቅሰዋል።
መከላከያ ሰራዊት ለአገር ሉዓላዊነት መጠበቅ የአገር የመጨረሻ ጋሻ በመሆኑ ሰራዊቱን በሁሉም መስክ ማጠናከር ዋነኛ አጀንዳ ተደርጎ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።
የአገር ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ይበልጥ ለማጠናከር በጥናት ላይ የተመሰረተ የክልሎች ልዩ ኃይሎች ወደ ፀጥታ መዋቅሮች እንዲደራጁ ተወስኖ መቆየቱን ገልፀው ተግባራዊነቱ ግን በተለያዩ አገራዊ ችግሮች መዘግየቱን አንስተዋል።
ውሳኔው የተማከለ የመከላከያ ሰራዊት መገንባት አስፈላጊ በመሆኑ መልሶ የሚደራጅ መሆኑን ገልፀው ትግበራውም በክልሎች የሚመለከታቸው የፖለቲካና የፀጥታ አካላት መግባባት ተደርሶበት በተመሳሳይ ጊዜ በሁሉም ክልሎች የሚፈፀም ነው ብለዋል።
ልዩ ኃይሎች ለአገር ሕልውና ማስጠበቅ ትልቅ ውለታ እንደነበራቸው ገልፀው ልዩ ኃይል አካላት በተቀመጠላቸው የተለያዩ አማራጮች መሰረት ዳግም የሚደራጁ መሆኑን ተናግረዋል።
የልዩ ኃይል አባላት የመከላከያ ሰራዊትና በክልሎች የፖሊስ ኃይል እንደየምርጫቸው መቀላቀል የሚችሉ ሲሆን ወደ መደበኛ ሕይወት ወይም ወደ ሲቪልነት መመለስ የሚፈልጉ ካሉ መንግሥት ተመላሾችን መልሶ የማቋቋም ሥራዎች ይሰራሉ ነው ያሉት።
በአንዳንድ አካባቢ በመረጃ እጦትና ትክክለኛ ዓለማውን ባለመገንዘብ ችግሮች እንዳሉ ገልፀዋል።
ትግበራው አገራዊ የኢኮኖሚ ሁኔታን ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን ጠቅሰው ሂደቱ ጥልቅ ጥናት የተደረገበት እንዲሁም የእያንዳንዱን ክልል ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ልዩ ኃይል የማደራጀት ሂደቱ ትጥቅ ማስፈታት ሳይሆን መልሶ ማደራጀት ነውም ብለዋል።
መልሶ የማደራጀት ሥራው በበጎ መልኩ የሚታይ ዕድል መሆን እንዳለበትና ሉዓላዊነትን የሚዳፈር ኃይል ለመከላከል ትልቅ አገራዊ ጥሪ መሆኑን ገልፀዋል።
ከሕወሓት ጋር በተያያዘ በሰላም ሥምምነቱ ሙሉ በሙሉ ትጥቅ የማስፈታት ሥራዎች ዓለም ከቀፍ ታዛቢዎች ባሉበት እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የሕወሓት ኃይሎችን ትጥቅ የማስፈታት ተልዕኮው ከክልሎች ልዩ ኃይል ዳግም የማደራጀት አገራዊ ዕቅዶች ጋር አብሮ የሚፈፀም አለመሆኑንም ጠቁመዋል።
በሁሉም ክልሎች ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ የአገር መከላከያ ሥምሪት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የልዩ ኃይል መልሶ ማደራጀት ተልዕኮው ከአገር ውስጥና ከውጭ ጥቃቶች የሚከላከል ጠንካራ የተማከለ ሰራዊቱ ለመገንባት ያለመ ነው ብለዋል።
በዚህም የተዛቡ መረጃዎችን መቀበልና መደናገር እንደማይገባ ጥሪ አቅርበዋል።
ከሸኔ የሽብር ቡድን ጋር በተያያዘ እየተካሄደ ባለው ኦፕሬሽን በርካታ አካባቢዎች ነፃ ወጥተው መደበኛ የመንግሥትና ማህበራዊ አገልግሎት ተጀምሯል ብለዋል።
የሰላም ጥሪውን ተከትሎ በርካታ የቡድኑ አባላት እጃቸውን እየሰጡ ወደ ተሃድሶ እየገቡ መሆኑን ገልፀው፤ መንግሥት ችግሩን በሰላም ለመፍታት ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሰራ አሁንም ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።