በአማራ ክልል ከ200 ሺህ ለሚበልጡ ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎት እየተሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ከ200 ሺህ ለሚበልጡ ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎት እየተሰጠ ነው
ባህር ዳር መጋቢት 29/2015 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በተያዘው የትምህርት ዘመን ከ200 ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ መርሀ ግብር ተጠቃሚ መሆናቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የስርዓተ ምግብ ባለሙያ አቶ ተዋበ ዓለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የተማሪዎች ምገባ መርሀግብር ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የምግብ አቅርቦት ክፍተት ባለባቸው አካባቢዎች ነው።
የምገባ መርሀግብሩ በማዕከላዊ ጎንደር እና በምስራቅ አማራ ስድስት ዞኖች በሚገኙ 402 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።
የምገባ አገልግሎቱ ተማሪዎቹ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ችግር ምክንያት በሚገጥማቸው የምግብ ችግር ትምህርታቸውን ሳያቋርጡ እንዲከታተሉ ማስቻሉን አብራርተዋል።
"በመርሀግብሩ ተማሪዎች የተመጣጠነ ምግብ እና ኃይል ሰጭ ብስኩት እዲያገኙ እየተደረገ ነው" ብለዋል።
አቶ ተዋበ እንዳሉት ለተማሪዎቹ የምገባ አገልግሎት እየተሰጠ ያለው በመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ትብብር ነው።
በክልሉ የትምህርት ቤት ምገባ የሚያስፈልጋቸው 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ተማሪዎች ቢኖሩም በበጀት እጥረት ምክንያት ሁሉንም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ አልተቻለም።
በመሆኑም በቀጣይ ምገባ ለሚያስፈልጋቸው የ1ኛ ደረጃ ተማሪዎች ተገቢውን በጀት በመመደብ ተደራሽነትን ለማስፋት በትኩረት መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
በዋግህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ የሽመድር 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ ካሳወት ደሴ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በትምህርት ቤቱ 964 ተማሪዎች የምገባ መርሀግብሩ ተጠቃሚ ናቸው።
የምገባ መርሀግብሩ መጀመሩ ዘንድሮ አንደኛ ክፍል የገቡ 154 ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይለዩ ከፍተኛ አስተዋጾ ማድረጉን ገልፀዋል።
መርሀ ግብሩ ተማሪዎች ሳያቋርጡ ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉና በትምህርት አቀባበላቸውም የተሻሉ እንዲሆኑ አግዟል።
"በትምህርት ቤቱ የምገባ መርሀግብር መጀመሩ ትምህርታችንን በአግባቡ ለመከታተል አግዞናል" ያለችው ደግሞ የእዚሁ ትምህርት ቤት ተማሪ ኤልዳና አቤል ናት።
"ከቤት በልተን የማንወጣ ተማሪዎች በትምህርት ቤቱ ስለምንመገብ ትምህርታችንን ሳናቋርጥ ለመከታተል ችለናል" ብላለች።
በአማራ ክልል በዘንድሮ የትምህርት ዘመን 4 ሚሊዮን የሚጠጉ የ1ኛ ደረጃ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።