መገናኛ ብዙኃን የሰላምና ዴሞክራሲ ግንባታን በማጎልበት ለአገር ብሔራዊ ጥቅም መስራት ይገባቸዋል - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙኃን የሰላምና ዴሞክራሲ ግንባታን በማጎልበት ለአገር ብሔራዊ ጥቅም መስራት ይገባቸዋል - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ
አዲስ አበባ መጋቢት 29/2015 (ኢዜአ)፦ መገናኛ ብዙኃን የሰላምና ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን በማጎልበት ለአገር ብሔራዊ ጥቅም መከበር በኃላፊነት ሊሰሩ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ አስገነዘቡ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር "መገናኛ ብዙኃን ለብሔራዊ ጥቅም" በሚል መሪ ሃሳብ የምክክር መድረክ በመካሄድ ላይ ነው።
በምክክር መድረኩም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፣ የተለያዩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ተቋማት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በዚሁ ወቅት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፤ ኢትዮጵያዊያን በየተሰማሩበት የስራ መስክ ሁሉ ስኬታማ ተግባራትን በማከናወን የአገርን ብሔራዊ ጥቅምና የዜጎችን ደህንነት አስጠብቆ ማስቀጠል ይገባቸዋል ነው ያሉት።
የአገር ብሔራዊ ጥቅም ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገር መቆየቱን ጠቁመው፤ ይህን ለማስቀጠልም መገናኛ ብዙኃን ለኢትዮጵያ ሰላም እና ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት መስራት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
አንጋፋው የሚዲያ ተቋም ኢዜአ በሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ የሚሰሩ የመገናኛ ብዙኃን የአገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ እንዲመካከሩ ማድረጉን አመስግነዋል።
መንግስት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አስጠብቆ ማስቀጠል የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ፈተናን በማሸነፍ እየተገኙ ያሉ የስኬት እና የተስፋ ሂደቶችን እጅ ለእጅ ተያይዞ በመሻገር የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት ስራዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።
የትኛውም አይነት የሃሳብ ልዩነቶች ቢኖሩ በሰከነ ውይይት እና ምክክር በመፍታት ለዜጎች አብሮነት እና አንድነት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
መገናኛ ብዙኃን ሰላም እና አንድነትን በማጽናት ለኢትዮጵያ ልማት እና ብሔራዊ ጥቅም መከበር መስራት እንደሚኖርባቸው ጠቁመው፤በድህረ ጦርነት ወቅትም የሽግግር ፍትሕን በማስፈን የአገርን ዘላቂ ሰላም እና ደህንነት ማጽናት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ፤ በበኩላቸው ኢዜአ በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ዜና እና ዜና ነክ ጉዳዮችን ተደራሽ በማድረግ ተዓማኒ የመረጃ ምንጭ ሆኖ እያገለገለ ነው ብለዋል።
በቀጣይም በ2022 ዓም የአፍሪካ ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ለመሆን በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ፣ በትግርኛ ፣ በእንግሊዝኛ እና በአረብኛ ቋንቋዎች ዜና እና ዜና ነክ ጉዳዮችን እያዘጋጀ ሲሆን በቅርቡም በፈረንሳይኛ ቋንቋም መረጃዎችን ለሕዝብ ማድረስ መጀመሩን ገልፀዋል።
በቅርቡም ተቋሙ ባስገነባው ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ በሙከራ ደረጃ በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ስርጭት እንደሚጀምር ጠቁመው፥ በሚቀጥለው መስከረም ወር የተሟላ የስርጭት አገልግሎት ለማስጀመር በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።