ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ፍትሃዊ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ሊጠናከሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ፍትሃዊ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ሊጠናከሩ ይገባል
አዲስ አበባ መጋቢት 29/2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ፍትሃዊ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ሲሉ የውሃና ኢነርጁ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ አመለከቱ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር 8ኛው የውሃ ዲፕሎማሲና ተግባቦት ላይ ያተኮረ ፎረም አካሂዷል።
በፎረሙ ላይ የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወካዮች ተሳትፈዋል።
በውይይቱም ላይ መነሻ ጹፎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞቿን ለመጠቀም ተፈጥሯዊ መብት ቢኖራትም በአንዳንድ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ሃሰተኛ ትርክት እንቅፋት የእገጠማት ነው።
በውጭ ጉዳይ አማካኝነት የውሃ ዲፕሎማሲ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው የዲፕሎማሲ ጥረቱ ውጤታማ እንዲሆን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ምሁራን ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመላክተዋል።
ውሃን በተመለከተ ጥናትና ምርምር ማድረግ፣ የተገኘውን ውጤት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማሳወቅ ከምሁራኑ የሚጠበቅ መሆኑንም አንስተዋል።
ይህንን ታሳቢ ያደረገ የተለያዩ ዩንቨርስቲዎችን ያካተተ ፎረም ከአንድ ዓመት በፊት መቋቋሙን ጠቅሰው በፎረሙ አማካኝነት ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በአባይ ጉዳይ ኢትዮጵያ ያላትን እውነት ለዓለም ማስተዋወቅ መገናኛ ብዙሃን የሚጠበቅ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአባይን ወንዝ ጨምሮ ከውኋ ሃብቶቿ በአግባቡ እንድትጠቀም በየዘርፉ ባለሙያዎችን ማፍራት ላይ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም አንስተዋል።
በዚሁ ማዕቀፍም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከአርባ ምንጭ፣ ባህዳር፣ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲዎችና ሌሎችም ዩኒቨርስቲዎች ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
በቀጣይም ውሃ ላይ ትኩረት አድርገው ከሚሰሩ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በጋራ ለመሥራትና ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ሥምምነት ለማድረግ ሚኒስቴሩ በሂደት ላይ ነው ብለዋል።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ደረጀ እንግዳ በበኩላቸው ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ የተጀመረው መነቃቃት በጥሩ ደረጃ ላይ ያለ ቢሆንም የበለጠ መሥራት ይጠይቃል።
እንደዚህ ዓይነት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም የአባይን ወንዝ ጨምሮ ኢትዮጵያ ያሏትን ሃብቶች በጥናት ላይ ተመስርታ እንድጥጠቀም ዕድል እንደሚፈጥር አብራርተዋል።