ቀጥታ፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ለገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉ ተቋማትን አመሰገነ

አዲስ አበባ መጋቢት 29/2015 (ኢዜአ)፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት ከ267 ሚሊዮን ብር ጀምሮ የተለያየ የገንዘብ መጠን ድጋፍ ያደረጉ ተቋማትን አመሰገነ።

ጽህፈት ቤቱ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መረጃ "የገበታ ለትውልድን ጥሪ ተቀብላችሁ ኃላፊነት ስለወሰዳችሁ፤ ለመጪው ትውልድ የምትመጥን ኢትዮጵያን ለመገንባት የድርሻችሁን ስላዋጣችሁ እናመሰግናለን" ብሏል።

ጽሕፈት ቤቱ በሶስተኛ ዙር ይፋ ያደረጋቸው ተቋማት ዝርዝር አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ቃል የገባውን 267 ሚሊዮን 50 ሺህ ብር ድጋፍ ሲያደርግ፤ የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ድርጅት እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እያንዳንዳቸው ቃል የገቡትን 50 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸው ተገልጿል።

በተጨማሪም ሰኢድ ያሲን ፒኤል ሲ ቃል ከገባው 30 ሚሊዮን ብር ላይ 20 ሚሊዮን ብር፣ ብሄራዊ ሎቶሪ አስተዳደር 12 ሚሊዮን 707 ሺህ 692 ብር ከ26 ሳንቲም፤ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ቃል የገባውን 10 ሚሊዮን 681 ሺህ 559 ብር ገቢ አድርገዋል።

እንዲሁም አልሳም ፒኤል ሲ፣ ታፍ ኦይል፣ አምደሁን ጠቅላላ ንግድ፣ ኤም ደብሌው ኤስ የንግድ ድርጅት ፣ ኤምሲጂ ኮንስትራክኝን ፒኤልሲ እና ጎልድ ውሃ እያንዳንዳቸው ቃል የገቡትን 10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም