በአሜሪካ የሚኖሩ ሁለት ትውልደ ኢትዮጵያውያን 7ሺህ መጻህፍትን ለአብርሆት ቤተ-መጻህፍት ለገሱ - ኢዜአ አማርኛ
በአሜሪካ የሚኖሩ ሁለት ትውልደ ኢትዮጵያውያን 7ሺህ መጻህፍትን ለአብርሆት ቤተ-መጻህፍት ለገሱ
አዲስ አበባ መጋቢት 29/2015(ኢዜአ)፦ በአሜሪካ የሚኖሩ ሁለት ትውልደ ኢትዮጵያውያን እህትማማቾች 7ሺህ መጻህፍትን ለአብርሆት ቤተ-መጻህፍት ለገሱ።
በእህትማማቾቹ ናኦሚ ተኮላ እና ክርስቲን ተኮላ የተሰበሰቡትን መጽሃፍት በአሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት ነዋሪ የሆኑት እናታቸው ወይዘሮ አያንቱ አበበ በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በመገኘት ለአምባሳደር ስለሺ በቀለ አስረክበዋል።
ልጆቻቸው የበጎ ስራ አርዓያ እንዲሆኑ ለማድረግ መጽሃፍትን የማሰባሰብ ስራ መጀመሩን ወይዘሮ አያንቱ ተናግረዋል።
የተለገሱት መጻህፍት የቋንቋ፣ የስነ-ህይወት፣ የታሪክ፣ የሂሳብ፣ የምርምር እና ሌሎች ዘርፎች ላይ ያተኮሩ እንደሆኑ ተገልጿል።
ዛሬ የተለገሱት መጻህፍት በኢትዮጵያ የንባብ ባህል እንዲዳብር ቤተ-መጻህፍት የተሟላ አቅርቦት እንዲኖራቸው ለማገዝ መሆኑን ወይዘሮ አያንቱ አስታውቀዋል።
በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ስለሺ በቀለ መጻህፍቱን በተረከቡበት ወቅት ትውልድን የሚያንጹ መጽሃፍት በመለገስ ለተደረገው አርዓያነት ያለው ስራ ምስጋና አቅርበዋል።
መጽሃፍቶቹን ከሌሎች መሰል የዳያስፖራ ወገኖች ከለገሷቸው መጻህፍት ጋር በማድረግ ለአብርሆት ቤተ-መጻህፍት እንደሚላክ መግለጻቸው ከኤምባሲው የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።