ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ መጋቢት 29/2015(ኢዜአ):- ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል።
በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰአት የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሲዳማ ቡና ይጫወታሉ።
በደረጃ ሰንጠረዡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ38 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ ሲቀመጥ ተጋጣሚው ሲዳማ ቡና በ19 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች አራት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
በአንጻሩ ሲዳማ ቡና ካለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዶ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር በሊጉ ባደረጉት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ 5 ለ 1 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ማሸነፉ ይታወቃል።
በሌላኛው መርሐ-ግብር አርባ ምንጭ ከተማ ከመቻል ከምሽቱ 12 ሰአት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
አርባ ምንጭ ከተማ በ18 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ሲገኝ ተጋጣሚው መቻል በ23 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
አርባ ምንጭ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፤ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል፤ ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
መቻል ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፎ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር የሊጉ መርሐ-ግብር ባደረጉት ጨዋታ አርባ ምንጭ ከተማ 2 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ18ኛ ሳምንት መርሐግብር እስከ ሚያዚያ 2 2015 ይቆያል።