ቀጥታ፡

በሕገ-ወጥ የወርቅና የተለያዩ ማዕድናት ፍለጋ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችና ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ሥር ዋሉ


አዲስ አበባ መጋቢት 28/2015(ኢዜአ)፦በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ወርቅና የተለያዩ ማዕድናት ፍለጋ ላይ የተሰማሩ የውጭ ሀገር ዜጎችና ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ። 

የፀና የጉዞ ሰነድ፣ የመግቢያ ቪዛ እንዲሁም የመኖሪያ ፍቃድ ሳይኖራቸው በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በጋምቤላ ክልል ወርቅና የተለያዩ ማዕድናት ፍለጋ ላይ የተሰማሩ 45 የውጭ ሀገር ዜጎችንና ሦስት ኢትዮጵያውያንን ከነ-ኤግዚቢቱ በመያዝ ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ ግብረ-ኃይሉ አስታውቋል፡፡


 

በተመሳሳይ ሁኔታ የፀና የጉዞ ሰነድ፣ የመግቢያ ቪዛ እንዲሁም የመኖሪያ ፍቃድ ሳይኖራቸው በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወርቅና የተለያዩ ማዕድናት ፍለጋ እንዲሁም የማምረት ስራ ላይ የተሰማሩ 47 የውጭ ሀገር ዜጎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ገልጿል።

በተጨማሪም ዘጠኝ ኃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ማኅበራትና ሰባት ኢትዮጵያውያን ግለሰቦችን ከእነ-ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝም የጋራ ግብረ-ኃይሉ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ሀገራችን ከማዕድን ዘርፉ ተጠቃሚ እንዳትሆን ማዕድናትን በኮንትሮባንድ ከሀገር እንደሚያወጡ ደርሼበታለሁ ያለው የጋራ ግብረ-ኃይሉ በህገ-ወጥ መንገድ በማዕድን ፍለጋ ላይ የተሰማሩ የውጭ ሀገር ዜጎች፣ ተባባሪ ኢትዮጵያውያን ግለሰቦችና ኃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ማኅበራት ላይ እያደረገ ያለው ጠንካራ ክትትል ከጋምቤላና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ባለፈ በሌሎች ክልሎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።


በሀገራችን የማዕድን ሃብት ላይ ያነጣጠረ ወንጀል በመፈፀም የተጠርጠሩ የውጭ ሀገር ዜጎች፣ ኢትዮጵያውያን ግለሰቦችና ኃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ማኅበራት ከነ-ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ሥር ሊውሉ የቻሉት በአካባቢው ኅብረተሰብ ጥቆማ መሠረት በተካሄደው ጠንካራ ክትትልና ኦፕሬሽን መሆኑም ተገልጿል።


ኅብረተሰቡ ላደረገው ቀና ትብብር የላቀ ምስጋናውን ያቀረበው የጋራ ግብረ-ሃይሉ በየትኛውም አካባቢ በሀገራችን ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጸሙ መሰል የወንጀል ተግባራትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ጥቆማ በመስጠት የሚያደርገውን ትብብር እንዲያጠናክር ጥሪውን አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም