ቀጥታ፡

የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር በኢትዮጵያ ከሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ መጋቢት 28/2015(ኢዜአ)፦የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።

ውይይታቸውም ሁለቱ ሀገራት በሳይበር ደህንነት ዙሪያ በጋራ በሚሰሩባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበረም ተገልጿል።

ዋና ዳይሬክተሩ የኢትዮጵያ መንግስት ከሩሲያ መንግስት ጋር በተለያዩ የልማት ዘርፎች እያከናወናቸው የሚገኘውን ጠንካራ የትብብር ስራዎች በሳይበር ደህንነት ዘርፍ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚፈልግም ለአምባሳደሩ ገልጸውላቸዋል፡፡

አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን በበኩላቸው ኢመደአ የኢትዮጵያን የሳይበር ደህንነት በማረጋገጥ የሀገሪቷን ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ እድገት ከመደገፍ አንፃር እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት አበረታች ናቸው ብለዋል።

በዚህም ሁለቱ ሀገራት ትብብራቸውን በሌሎች የልማት ዘርፎች እንደሚያደርጉት ሁሉ በሳይበር ደህንነት ዙሪያም በመድገም የተጠናከረ ስራ መስራት እንዳለባቸውና ለዚህ ስኬትም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም