እድርና እቁብ የመሳሰሉ ማህበረሰብ ተኮር ባህሎች  ለኢኮኖሚ እድገት አቅም የሚሆን የቁጠባ ባህልን የማዳበር ሚናቸው የላቀ ነው - ምሁራን 

621

ጂንካ መጋቢት 28 / 2015 (ኢዜአ).ዕድርና  ዕቁብ የመሳሰሉ ማህበረሰብ ተኮር ባህሎች መጠናከር ለኢኮኖሚ እድገት አቅም የሚሆን የቁጠባ ባህልን  የማዳበር ሚናቸው የጎላ መሆኑን ምሁራን አመለከቱ ።

በጂንካ ዩኒቨርስቲና በጀርመኑ ፍራንክፈርት ፎርቪኒየስ ኢንስቲትዩት በተዘጋጀ አውደ-ጥናት ላይ በኢትዮጵያ፣ ዱባይ፣ እስራኤልና ሌሎች ዓለም አገራት እንደ እድርና ዕቁብ በመሳሰሉ ማህበረሰብ ተኮር ባህሎች እንዲሁም  በብድርና ቁጠባ ተቋማት ላይ የተሰሩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።

የጂንካ ዩኒቨርስቲ  የተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አለሙ አይሌቴ በአውደ ጥናቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ዩኒቨርስቲው ከመማር ማስተማር ስራ ጎን ለጎን የአካባቢውን ማህበረሰብ የቁጠባ ባህል በማሳደግ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ነው ።

ዛሬ እየተካሄደ ያለው በቁጠባ ባህል ማሳደግ ላይ ዓለም አቀፍ ተሞክሮን ያካተተ አውደ-ጥናትም ዩኒቨርስቲው ማህበረሰቡን በተለያየ መንገድ ተጠቃሚ ለማድረግ ከሚሰራቸው የማህበረሰብ ተኮር የአቅም ግንባታና የጥናትና ምርምር ስራዎች አካል መሆኑን አመልክተዋል ።

በተለይም በአካባቢው የሚገኘው አርብቶና አርሶ አደር ያለውን ሀብትና ጸጋ በአግባቡ በመጠቀምና በመቆጠብ ተጠቃሚነቱን እንዲያረጋግጥ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ዩኒቨርሲቲው በጥናትና ምርምር ስራዎች ለማህበራዊ ችግሮች የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ከማመላከት በተጨማሪ የማህበረሰቡን አቅም በማሳደግ ኑሮው እንዲሻሻል ማስቻል  ከሚሰራባቸው የትኩረት መስኮች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

"በግብርና፣ በብዝሀ ባህልና በመሳሰሉት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የጥናት መስኮች ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየሰራን ነው" ብለዋል።

ዶክተር አለሙ አክለው በማህበረሰቡ እንደልምድ የተያዙ ዕድር፣ እቁብና መሰል ማህበራዊ መሰረቶችን በማጠናከር ለላቀ የቁጠባ ባህል መጎልበትና ለኢኮኖሚው እድገት መጠቀም እንደሚገባ ጠቁመው ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

በአውደ-ጥናቱ  የተሳተፉት የቀድሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርና ተመራማሪ እና በኢትዮጵያ ያንግ ላይት የጥናት ፕሮጀክት ዳይሬክተር ዶክተር አሉላ ፓንክረስት ማህበረሰብ የሚከወኑ እንደ እድርና እቁብ የመሳሰሉ ማህበረሰባዊ ተቋማት ለቁጠባ ባህል መጎልበት ሚናቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል ። 

የዛሬው አውደ ጥናትም በጅንካና ጀርመን አገር በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ትብብር የቁጠባ ባህልን አስመልክቶ በማህበረሰብ ተኮር ስላለው አበርክቶ የተጠኑ አለም አቀፍ የጥናት ውጤቶች የቀረቡበትና ተሞክሮ የሚወሰድበት መሆኑን ተናግረዋል። 

ዕድር በተለይም ዕቁብ የመሰሉ ማህበራዊ መስተጋብሮች በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓና በኤዥያም የሚዘወተሩ እንደሆኑ የጠቆሙት ዶክተር አሉላ በተለይም እቁብ በሌሎች የዓለም ክፍሎች በስፋት የሚዘወተርና የቁጠባ ባህልን ለማዳበር የጎላ ሚና ያለው ስለመሆኑ አመልክተዋል።

በተለይ ከኢትዮጵያ ወደ ሌሎች ውጭ አገራት የሚሄዱ ዲያስፖራዎች ማህበራዊ ግንኙነታቸውን ጭምር ለማጠናከርና የቁጠባ ባህላቸውን ለማሳደግ ከሚጠቀሙባቸው ስልቶች አንዱ ዕድር እና ዕቁብ የመሳሰሉ ማህበራዊ መስተጋብሮች መሆናቸውን ጠቁመው ማህበራዊ መስተጋብሮቹን በመጠቀም የቁጠባ ባህላቸውን ማጎልበት እንደቻሉ አመልክተዋል ።

ማህበራዊ መስተጋብሮቹ ማህበራዊ ግኑኝነትን ለማጠናከር፣ የቁጠባ ባህልን ለማሳደግ ብሎም የማህበረሰብ ልማቶችን ለማፋጠንና ሀገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገትን ለመደገፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው በመሆኑ መጠናከር እንዳለባቸው ዶክተር አሉላ  አስገንዝበዋል ።

በኢትዮጵያ የፕራንክፐርት ፎርቪኒየስ ኢንስቲትዩት ተመራማሪ ዶክተር ሶፊያ ቲቮቪል በበኩላቸው "ኢንስቲትዩቱ ዕድር እና ዕቁብ የመሳሰሉ ማህበራዊ ተቋማት ለዘመናዊ የቁጠባ ባህል መጎልበትና ለዜጎች ኑሮ መሻሻል ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ማሳየት ዓላማ አድርጎ እየሰራ ነው "ብለዋል ።

ማህበራዊ መስተጋብሮቹ ተጠናክረው የሚቀጥሉበትን መንገድ ማመላከት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንንአመልክተዋል። 

የማህበረሰብ መሰረቶች የሆኑ የዕድር እና ዕቁብ መጠናከር ለዜጎች ኑሮ መሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ ያላቸው መሆናቸውን ጠቅሰው ማህበራዊ አንድነትንና የእርስ በእርስ ትስስርን የሚያጠናክሩ ከመሆናቸው ባለፈ ለሀገራዊ የልማት ጥያቄ ምላሽ ቀጣይነት አቅም እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

በደቡብ ኦሞ ከሚገኙ ማህበራዊ የብድርና ቁጠባ ተቋማት አንዱ ከ200 በላይ መምህራንን አቅፎ በ1997 ዓ.ም የተቋቋመው የዞኑ መምህራን ማህበር ብድርና ቁጠባ ተጠቃሽ ነው።

የማህበሩ ሰብሳቢ መምህር ስሜ ማነኩል የመምህራን ማህበሩ ከትንሽ ካፒታል ተነስቶ በአሁኑ ሰዓት ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያለውና ለበርካታ መምህራን ኑሮ መሻሻል ትልቅ አስተዋጾ እያበረከተ ያለ መሆኑን ተናግረዋል ።

የቁጠባ ባህል የዘመናዊነት መገለጫና የነገ ብሩህ ተስፋዎች ዕውን ማድረጊያ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመልክተዋል ።

በአውደ ጥናቱ ከኢትዮጵያ ጂንካ፣ ሀዋሳና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች የተለያዩ ጥናት አቅራቢዎች የተሳተፉ ሲሆን ከውጭ አገራት ደግሞ ከጀርመኑ ፍራንክፈርት ፖርቪኒዬስ ኢንስቲትዩት እና ከሌሎች የምርምር ተቋማት የመጡ ጥናት አቅራቢዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው ።

እንዲሁም ከአከባቢው የተውጣጡ የዕድርና ብድር ተቋማት ተወካዮች እየተሳተፉ ነው። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም