የታችኛው የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ኢትዮጵያ ለወንዙ ዘላቂ ፍሰት እያከናወነች ያለውን የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ሊያግዙ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የታችኛው የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ኢትዮጵያ ለወንዙ ዘላቂ ፍሰት እያከናወነች ያለውን የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ሊያግዙ ይገባል
አዲስ አበባ መጋቢት 28/2015 (ኢዜአ) የታችኛው የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ኢትዮጵያ ላይ ከሚያነሱት ምክንያታዊ ያልሆኑ ጥያቄዎች ወጥተው ለወንዙ ዘላቂ ፍሰት የሚበጁ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን ሊያግዙ እንደሚገባ የባሕር ዳር እና የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች ተናገሩ፡፡
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኝ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በዓባይ ወንዝ እና በጣና ተፋሰስ ላይ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች ላይ ሰፊ ጥናትና ምርምሮችን አድርጓል።
ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የጥናት ዘዴዎች ለፖሊሲ ግብዓት የሚውሉ የምርምር ሥራዎችን በማካሄድ ከአሥር ዓመታት በላይ የሆኑ መረጃዎችን ማጠናቀሩን ተናግረዋል።
በተለይም ደለልን በመከላከል የሕዳሴ ግድብን አገልግሎት በሦስት እጥፍ ለማራዘም የሚያስችሉ ምክረ- ሃሳቦችን የያዙ መረጃዎች ማውጣቱን ነው ያነሱት።
በተመሳሳይ በዓባይ ተፋሰስ ላይ የሚሰራው የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ታፈረ መላኩ፤ ዩኒቨርሲቲው በጥናት፣ በምርምርና በማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት የሚያከናውናቸው ሥራዎች ከተፋሰሱ ስፋት አንጻር በቂ እንዳልሆነ ያነሳሉ።
ከሦስት ዓመታት በፊት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የ'ጮቄ ስምምነት' በሚል የዓባይ ተፋሰስ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች ላይ በጋራ ለመሥራት ግብ ማስቀመጣቸውንም አስታውሰዋል፡፡
የተቀመጠውን የጋራ ግብ ለማሳካት በሚፈለገው ልክ እየተገበሩ አለመሆኑንም አንስተዋል፡፡
የዓባይ ተፋሰስ ላይ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች በቅጡ አለመከናወን በወንዙ ፍሰት መጠን ላይ አሉታዊ ጫና እንደሚያሳድር ነው የተናገሩት፡፡
በመሆኑም የታላቁ ሕዳሴ ግድብን የአገልግሎት ዘመን ለማራዘም፣ ብሎም የወንዙን ዘላቂ ፍሰት ለመጠበቅ፣ የምርምር ተቋማት በጋራ መሥራትና የተፋሰሱን የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ለመጭው ትውልድ እንዲውል ለማድረግ ብሎም ለዓባይ ወንዝ ዘላቂ ፍሰት በላይኛው ተፋሰስ ላይ የሚሰሩ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች የማይተካ ሚና እንዳላቸው ፕሬዝዳንቶቹ ያነሳሉ።
የተፋሰስ ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያነሱት ስጋት ኢትዮጵያ ከወንዙ እንዳትጠቀም እንጂ የዓባይ ውሃ ፍሰት በዘላቂነት እንዲኖር አብሮ ለመሥራት አስበው አያውቁም ሲሉ ይተቻሉ።
ይህም ተቃውሟቸው ሳይንሳዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ አንስተዋል።
በርካታ ወንዞች ከጊዜ ብዛትና ከአካባቢ መራቆት መቀነሳቸውን የሚያነሱት ዶክተር ታፈረ፤ በወንዙ ፍሰት ዘላቂነት ኢትዮጵያ ለምታከናውነው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ የተፋሰሱ ሀገራት መደገፍና መተባበር ይገባቸዋል ብለዋል።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የችግሩ አሳሳቢነት ላይ ጥናቶችን ማሳተም እንዲያጠናክሩ፤ የታችኛው እና የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎችም በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ነው ያነሱት።