ቀጥታ፡

የብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ 500 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ሊያካሂድ ነው

አዲስ አበባ መጋቢት 28/2015(ኢዜአ)፦ የብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ የሚውል 500 ሚሊየን ብር ድጋፍ መሰብሰብ የሚያስችል የቦንድ ግዥ መርሐ ግብር በመጪው ቅዳሜ በድሬደዋ እንደሚጀምር አስታወቀ።

የወጣቶች ሊግ ምክትል ፕሬዚደንት እና የጽህፈት ቤት ኃላፊዋ ኦባንግ ኩመዳን፤ ወጣቶች የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብርን ጨምሮ በልዩ ልዩ አገራዊ የልማት ስራዎች ላይ የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የብልጽግና ወጣቶች ሊግ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ አባላት እንዳሉት ጠቅሰው፥ ወጣቱን በማነቃነቅ 500 ሚሊየን ብር ድጋፍ መሰብሰብ የሚያስችል የቦንድ ሽያጭ መርሐ ግብር በሚቀጥለው ቅዳሜ በድሬደዋ ከተማ እንደሚጀምር ገልጸዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፥ ወጣቶችም ለሰንደቅ ዓላማ ፕሮጀክታቸው የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር  ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

በድሬደዋ ከተማ በሚጀምረው የገቢ ማሰባሰብ መርሐ ግብር ከ300 ብር ጀምሮ የቦንድ ሽያጭ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም