በሰሜን ጎንደር ከበለስ-መካነ ብርሃን ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የአስፓልት መንገድ ግንባታ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ጎንደር ከበለስ-መካነ ብርሃን ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የአስፓልት መንገድ ግንባታ እየተካሄደ ነው
ባህርዳር መጋቢት 28/2015 (ኢዜአ) በሰሜን ጎንደር ዞን ከበለስ-መካነ ብርሃን ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የጥራት ደረጃውን የጠበቀ የአስፓልት መንገድ እየተገነባ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።
በአስተዳደሩ የጎንደር ኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ማኔጅመንት ቢሮ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ብሩክ አዳነ እንደገለጹት፣ የአስፓልት መንገዱ ሲጠናቀቅ ደባርቅ ከተማን ከጃናሞራ ወረዳ ለማገናኘት ያስችላል።
መንገዱ 39 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዳለውና በመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ሥራ ተቋራጭነት እየተገነባ መሆኑንና ሙሉ ወጪው በመንግስት እንደሚሸፈን ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል።
የመንገዱ ግንባታ እየተከናወነ ያለው መልክአ ምድሩ አስቸጋሪ በሆነ ቦታ ቢሆንም በተገባው ውል መሰረት ግንባታው እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
በመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ የሚገኙ ድልድዮች አብዛኛቹ በመገንባታቸው የአካባቢው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ከወዲሁ እየተነቃቃ መሆኑን አስረድተዋል።
የመንገዱ ግንባታ ሲጠናቀቅ የአካባቢውን የሰብልና የእንስሳት ምርት በቀላሉ ወደ ገበያ ለማድረስና የህብረተሰቡን የእርስ በእርስ ግንኙነት ለማጠናከር ፋይዳው የጎላ ነው ሲሉ ኢንጂነር ብሩክ ገልጸዋል።
የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ሰሎሞን ደመቀ በበኩላቸው፣ መንገዱ የአካባቢውን አስቸጋሪ መልከዓ ምድር በመቋቋም ደረጃውን ጠብቆ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ግንባታውን ለማፋጠን ማሽነሪዎችና የግንባታ መሳሪያዎች በበቂ ሁኔታ እንዲገቡ መደረጉንም ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ አፈጻጸም 60 በመቶ መድረሱን ጠቁመው፣ ግንባታውን በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በበለስ ኮንሰልቲንግ ፒኤልሲ የበለስ መካነ ብርሃነ ፕሮጀክት ተጠሪ መሃንዲስ ኢንጂነር ይላቅ ካሳሁን እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ በተቀመጠው የጥራት ደረጃ መሰረት እንዲከናወን ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ነው።
ከሚገነቡ 10 ድልድዮች ውስጥ የስምንቱ ግንባታ መከናወኑን ጠቁመው የመሬት ቆረጣ፣ የአፈር ሙሊትና ሌሎች ሥራዎችም እየተከናወኑ መሆኑን አመልክተዋል።
የመንገድ ፕሮጀክቱ እስከ 600 ለሚደርሱ የአካባቢው ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም ኢንጂነር ይላቅ ገልፀዋል።
የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ዜጎች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ከመሆን በላይ የእውቀትና የክህሎት ሽግግር እያገኙ መሆኑንም አመልክተዋል።
"በመንገድ ፕሮጀክቱ በቀን ሠራተኝነት ብቀጠርም አሁን ላይ የሚክሰር ኦፕሬተር ባለሙያ ሆኛለሁ" ያለችው ደግሞ በፕሮጀክቱ የሥራ ዕድል የተፈጠረላት ወጣት እናኔ አንተሌ ናት።
በሥራ ሂደት ያገኘችውን አዲስ እውቀትና የሥራ ልምድ በመጠቀም በቀጣይ የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን እንደምትሰራም ገልጻለች።
ከሚከፈላት ደመወዝ የራሷን መኖሪያ ቤት መስራቷንና በቀጣይ ቤተሰቦቿን ለመጥቀም ጠንክራ እንደምትሰራ ተናግራለች።
በሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ታስቦ በ2009ዓ.ም የተጀመረው የመንገዱ ፕሮጀክት በተለያዩ ምክንያቶች ቢዘገይም አሁኑ ላይ ያንን በሚያካክስ መልኩ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።