ቀጥታ፡

የትምህርት ተቋማት ለኢንዱስትሪ ልማት የሚኖራቸውን ሚና ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው- የትምህርት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ መጋቢት 28/2015(ኢዜአ)፦የትምህርት ተቋማት ለኢንዱስትሪ ልማት የሚኖራቸውን ሚና ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

ለኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማት እድገት የትምህርት ተቋማትን አበርክቶና እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን በተመለከተ በትምህርት ሚኒስቴር የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሰለሞን ቢኖር ጋር ኢዜአ ቆይታ አድርጓል።

የትምህርት ተቋማት ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ልማትና እድገት ግንባር ቀደም መሆን እንዳለባቸው ዶክተር ሰለሞንይናገራሉ።

በተለይም የኢንዱስትሪ ልማት የጥናትና ምርምር እንዲሁም የፈጠራ ሥራዎችን የሚጠይቅ በመሆኑ የትምህርት ዘርፉ ድርብ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን ገልጸዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር በሕግ ከተሰጠው ሥልጣን ውስጥ አንዱ የትምህርትና ሥልጠና፣ ምርምር ተቋማትና የኢንዱስትሪ ትስስርን በሀገር አቀፍ ደረጃ ማጠናከር በመሆኑ፤ በዚሁ ዙሪያ በስፋት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሁሉም መስክ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማከናወን ለአገር አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በተለይ ደግሞ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ የምርምር ሥራዎች በተጠናከረ መልኩ መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ በመሆኑ ለዘላቂነቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እገዛ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል። 

ለኢንዱስትሪው እድገትና ምርታማነት የድጋፍና ምርምር ሥራዎች ይቀጥላሉ ነው ያሉት ዶክተር ሰለሞን። 

በኢትዮጵያ የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ልማት፣ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ኩታገጠም ልማት እንዲሁም አዳዲስ በውጤት ላይ የተመሠረተ የኢንዱስትሪ ማበረታቻ ጭምር በመንግሥት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም