ለተሰበረው የጀማ ወንዝ የብረት ድልድይ መፍትሄ ለመስጠት የባለሙያዎች ቡድን ወደ ስፍራው ተልኳል--አስተዳደሩ - ኢዜአ አማርኛ
ለተሰበረው የጀማ ወንዝ የብረት ድልድይ መፍትሄ ለመስጠት የባለሙያዎች ቡድን ወደ ስፍራው ተልኳል--አስተዳደሩ

ደብረ ብርሀን መጋቢት 28/2015(ኢዜአ)፦ በአማራ ከልል ሰሜን ሸዋ ዞን ለተሰበረው የጀማ ወንዝ የብረት ድልድይ መፍትሄ ለመስጠት የባለሙያዎች ቡድን ወደ ስፍራው መላኩን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።
በጀማ ወንዝ ላይ የሚገኘውና 100 ሜትር ርዝመት ያለው የብረት ድልድይ ትናንት ከሰዓት በኋላ የመሰበር አደጋ እንዳጋጠመው በአስተዳደሩ የደብረ ብርሀንና አካባቢው የፕሮጀክት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ንጋቱ ውድነህ ለኢዜአ ገልጸዋል።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ ድልድዩ የተሰበረው ሁለት ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች በአንድ ጊዜ በድልደዩ ላይ ተከታትለው ለማለፍ ሲሞክሩ ነው።
"በድልድዩ መሰበርም ከአዲስ አበባ-መርሃ ቤቴ-ሚዳ-ደጎሎ የትራንስፖርት አገልግሎቱ ከትናንት አመሻሽ ጀምሮ ተቋርጧል" ብለዋል።
የጀማ ወንዝ የብረት ድልድዩ ከ20 ዓመት በላይ አገልግሎት የሰጠ መሆኑንም አቶ ንጋቱ ጠቅሰዋል።
የተስተጓጎለውን የትራፊክ ፍሰት ፈጥኖ በመፍታት አገልግሎቱን ለማስቀጠል ትናንት ወደ አመሻሽ የባለሙያዎች ቡድን ተልኮ ተለዋጭ መንገድ የማመቻቸት ሥራ መጀመሩን አመልክተዋል።
እንዲሁም ከኮብ መስክ-መርሃ ቤቴ-ሚዳ ደጎሎ ያለው የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ሥራ ላይ የነበሩ ማሽነሪዎችን በማስገባት ለችግሩ እልባት ለመስጣት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ነው የገለጹት።
ድልድዩ ለትራንስፖርት እንቅስቃሴው ወሳኝ በመሆኑ የክረምት ወራት ከመግባቱ በፊት ለህብረተሰቡ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ከተለዋጭ መንገድ ሥራ ጎን ለጎን ጥገና እንደሚካሄድም ገልፀዋል።
በስፍራው የደረሰው የኮንስትራክሽን ባለሙያዎችን ያካተተ ቡድን የጥገና ሥራ መጀመሩን ጠቁመዋል።
ተለዋጭ መንገዱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተሰርቶ እስኪጠናቀቅ ድረስ ህብረተሰቡ በትግስት እንዲጠባበቅም አቶ ንጋቱ ጠይቀዋል።