ቀጥታ፡

የክልሉ መንግሥት ሰራተኞች ለህዳሴ ግድብ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ

ሀዋሳ መጋቢት 28/2015 (ኢዜአ):- የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው  የደቡብ ክልል የመንግሥት ሰራተኞች ገለጹ።

የክልሉ የመንግሥት ሰራተኞች እንዳሉት፤ ከለውጡ ወዲህ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ በተሰጠው ትኩረት አሁን ያለበት ደረጃ ላይ መድረሱ አስደስቷቸዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ሰራተኛ አቶ አብርሃም ዓለሙ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ኃይል ከማመንጨት ባለፈ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ትርጉም ያለው ፕሮጀክት እንደሆነ ገልጸዋል።

ትውልዱ የዓባይን ግድብ ገንብቶ በማጠናቀቅ የራሱን የታሪክ አሻራ የሚያኖርበት ፕሮጀክት እንደሆነም  ተናግረዋል።

ለግንባታውም አምስት ጊዜ ቦንድ በመግዛት፣ ህብረተሰቡን የመቀስቀስና “በ8100 A” አጭር የጽሁፍ መልዕክት በመላክ የድርሻቸውን ለመወጣት ጥረት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ሌላው የምክር ቤቱ ሰራተኛ አቶ ሀብታሙ ኮርማ በበኩላቸው ግድቡ ሲጀመር መላው ኢትዮጵያውያን ከዳር ዳር በመነሳት ለግንባታው ያላቸውን ድጋፍ ሲገልጹ እንደነበር አስታውሰዋል።


 

አክለውም ግድቡ እስካሁን ያጋጠሙትን ፈተናዎች ተሻግሮ አሁን ተስፋ ሰጪ ደረጃ ላይ መድረሱ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።

ግንባታው አሁን ያለበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ባለፉት አራት ዓመታት በውጤት በመታጀቡ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ሞራልና ደስታ መፍጠሩን ገልጸዋል።

የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስም ቦንድ መግዛታቸውን አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ ጠቁመዋል።

ወይዘሮ ሰብለወርቅ አበራ በበኩላቸው ለግድቡ ግንባታ የሚያደርጉት ድጋፍ ሀገራዊ ግዴታቸው እንደሆነ ገልጸዋል።


 

"እጅ ለእጅ ከተያያዝን ያለንን ሀብት ልንጠቀም እንችላለን" ያሉት አስተያየት ሰጪዋ፤ ትውልዱ አሻራ ማኖር እንደሚችል ሰርተን ማሳየት አለብን ብለዋል።

ለዚህም "እስካሁን በአምስት ዙር ቦንድ ገዝቻለሁ በቀጣይም እስኪጠናቀቅ በቦንድ ግዢም ሆነ በማንኛውም መንገድ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ " ሲሉ ገልጸዋል።

የደቡብ ክልል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ሚልክያስ እስራኤል እንዳሉት፤ የክልሉ ህዝቦች ለግድቡ ግንባታ ከጅምሩ አንስቶ ድጋፍ እያደረጉ ነው።


 

የህብረተሰቡን ተሳትፎ ለማጠናከርም የተለያዩ አደረጃጀቶችና አማራጮች በማመቻቸት እየተሰራ ነውም ብለዋል።

ኹነቶችን በየዓመቱ በማዘጋጀት ህዝቡ ድጋፍ እንዲያደርግ የቦንድ፣ የደረት ባጅ ሽያጭና የ8100 A አጭር የጽሁፍ መልዕክት ማስተላለፊያ መንገድን በመጠቀም ገቢ ሲሰባሰብ መቆየቱን  አስታውሰዋል። 

በዚህም ባለፉት 11 ዓመታት ከቦንድና ከደረት ባጅ ሽያጭ እንዲሁም ከ8100 አጭር የጽሁፍ መልዕክት ከክልሉ ከ1 ቢሊዮን 301 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ገልጸዋል።

የህዳሴ ግድብ መሰረት የተቀመጠበትን 12ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ “ግድባችን የአንድነታችን ብርሃን ነው” በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ አካባቢዎች ዕለቱ ታስቦ እንዲውል በማድረግ ከ5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም