ቀጥታ፡

የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የቦንድ ግዥ ንቅናቄ አስጀመረ

አዳማ  መጋቢት 28/2015(ኢዜአ)፡-የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ  የ300 ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዥ ንቅናቄ አስጀመረ።

በሊጉ የአደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊና የማዕከላዊ ኮሚቴው አባል ወይዘሮ አሰገደች ደሴ ለኢዜአ  እንደገለፁት ግድቡ አሁን የሚገኝበት ምዕራፍ ወሳኝ በመሆኑ ልዩ ድጋፍ ያስፈልጋል።

የግድቡ መጠናቀቅ በተለይም የሴቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ከመፍታት አንፃር ጉልህ ሚና እንዳለው በማውሳት።

በመብራት እጦት በገጠርና ከተማ ያሉ የእናቶቻችን ችግር የሚያቃልል መሆኑን ጠቅሰው ግንባታው ከተጀመረበት ዕለት ጀምሮ ሴቶች እያደረጉ ያለው ርብርብ አሁንም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ትናንት በይፋ በአዳማ አባገዳ አዳራሽ ከስራ ግምገማ ውይይታቸው ጎን ለጎን የተጀመረው የቦንድ ግዥ ንቅናቄ እስከ መጪው ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም የሚቆይ ይሆናል ብለዋል።


 

በዚህም ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ ንቅናቄ መጀመራቸውን ነው ወይዘሮ አሰገደች የገለጹት።

በቦንድ ግዢው ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት የሊጉ አባላት ይሳተፋሉ ያሉት ሃላፊዋ፤ ለስኬቱም ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ ያሉ የሊጉ አመራሮች በግንባር ቀደምትነት የማስተባበር ሚናቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

በቦንድ ግዢ ንቅናቄው ከሊጉ አባላት ውጪ ባለሃብቶችን ጨምሮ የተለያዩ የሴቶች አደረጃጀቶችም ይሳተፋሉ ብለዋል።

በቦንድ ግዢው የተጀመረውን ግድብ በማጠናቀቅ የሴቶችን የስራ ጫናና እንግልት ከመፍታት ባለፈ የሴቶች የቁጠባ ባህል ለማዳበር ያለመ ንቅናቄ መሆኑንም አመልክተዋል።

የጨፌ ኦሮሚያ አፈጉባኤና የሊጉ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱራህማን በበኩላቸው በክልሉ የሴቶችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብለዋል ።


 

በዚህም ሴቶች ይመራሉ ተብሎ የማይታመነውን ተቋማትና የአስተዳደር ዘርፍ ጨምረው እየመሩ ይገኛሉ ያሉት ወይዘሮ ሰዓዳ፤ ይሄ የለውጡ ውጤትና ሊጉ ሴቶችን በአቅም እያበቃ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።

የክልሉን ሴቶች ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ለማላቀቅ ከሲንቄ ባንክ ጋር በትብብር ከመስራት ባለፈ ከቀበሌ ጀምሮ የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

የተጀመረው የቦንድ ግዥ ንቅናቄም የህዝቦች የጋራ አሻራ የሆነውን የህዳሴ ግድብ ከዳር ከማድረስ ባለፈ የሴቶችን የቁጠባ ባህል ለማጎልበት ጉልህ ድርሻ አለው ብለዋል።

የክልሉ ህዝብ በ2014 ዓ.ም ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ  ማድረጉንም አስታውሰው፤ በዚህም የሴቶች ተሳትፎ 50 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል።

በንቅናቄው የሊጉን የቦንድ ግዥ ለማሳካት በተለይም ሁሉም የኢትዮጵያ ሴቶች ተሳትፎ እንዲያደርጉም ሊጉ ጥሪ አቅርቧል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም