ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለስልጣን የጨረራ አመንጪ መሳሪያዎች አጠቃቀምና አወጋገድ ቁጥጥርን ማጠናከር አለበት-የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ

አዲስ አበባ መጋቢት 27/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለስልጣን የጨረራ አመንጪ መሳሪያዎች አጠቃቀምና አወጋገድ ላይ የሚያደርገውን ቁጥጥር ማጠናከር እንዳለበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ባለሥልጣኑ ጨረራ አመንጪ መሳሪያዎች ጥቅም ላይ በሚውሉበት ጊዜ ለዜጎች ደህንነት ቅድሚያ እንዲሰጥ የወጡ ህግጋትና መመሪያዎችን በአግባቡ ስራ ላይ ማዋል አለበት ተብሏል።

ቋሚ ኮሚቴው በኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለስልጣን የጨረራ አመንጪ ቁሶች ፈቃድ አሰጣጥ እና የቁጥጥር አፈጻጸምን በተመለከተ 2013/14 የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ተወያይቷል። 

በውይይቱ ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር በባለሥልጣኑ አሰራር ላይ በተስተዋሉ የኦዲት ግኝቶች ላይ ማብራሪያ አቅርቧል።  


 

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሰረት ዳምጤ እንደተናገሩት፤ የጨረራና ኒውክሌር መከላከያ አዋጅ ቁጥር 1025/2009 መሰረት በማድረግ የጨረራ አመንጪዎች መሳሪያዎችን በሚመለከት የማሳወቅና ፈቃድ የማግኘት ግዴታዎች፣ እንዲሁም ቁጥጥርና ክትትልን የሚመራ ደንብ አለመውጣቱን ገልጸዋል።

ባለስልጣኑ ህጋዊ አሰራርን ሳይከተል እና ደንብ ሳያወጣ ፈቃድ ከመስጠት ጀምሮ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን በኦዲት ግኝቱ ተለይቷል ነው ያሉት።  

የመስሪያ ቤቶች ጨረራ አመንጪ ቁሶች አያያዝ እና አጠቃቀምን በተመለከተ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቱ በናሙና በመረጣቸው ተቋማት ላይ ቅኝት ያደረገ ሲሆን ጉድለቶች መኖራቸው ተረጋግጧል ብለዋል።

በጨረራ ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች የጤና ምርመራ ማድረግ እንዳለባቸው በመመሪያው ላይ ቢቀመጥም የአፈጻጸም ውስንነት መኖሩን አይተናል ሲሉም ነው የገለጹት።

የመንግሥትም ይሁን የግል ሆስፒታሎች ጨረራ አመንጪ መሳሪያዎች ሲያስጠግኑም ሆነ ሲያስወግዱ ባለስልጣኑ እንዲያውቀው ማድረግ ላይ ሰፊ ክፍተት እንዳለ የጠቆሙት ዋና ኦዲተሯ፤ ይህም በህብረተሰብ ጤና ላይ ትልቅ ችግር ሊያመጣ የሚችል በመሆኑ ትኩረት እንደሚያስፈልገው አስረድተዋል።


 

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ምክትል ዋና ኦዲተር አቶ አበራ ታደሰ በበኩላቸው ባለስልጣኑ የጨረራ ዝቃጭ ቁሶች አወጋገድ እና ደህንነት ፖሊሲ ለማጸደቅ የያዘው እቅድ መራዘሙን ጠቁመው ፖሊሲው ጸድቆ በፍጥነት ወደ ስራ መግባት አለበት ነው ያሉት።

ምክትል ዋና ኦዲተሩ እንዳሉት፤ የጨረራና ኒውክለር ቁጥጥር ባለሥልጣን ማቋቋሚያ ደንብን እና ሌሎች ህጎችን በሚገባ ለማስፈጸም ከተዘጋጁ 13 መመሪያዎች መካከል ወደ ሥራ የገቡት ሦስት ብቻ መሆናቸው በኦዲት መረጋገጡን ጠቅሰዋል።

እነዚህ መመሪያዎች ባለሥልጣኑ ወጤታማ ሥራ እንዲያከናውን የሚያግዙ በመሆናቸው ያልጸደቁ መመሪያዎችን በፍጥነት ማጸደቅ ላይ ትኩረት እንዲሰጥ አመልክተዋል። 


 

የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፤ ያለፈቃድ ጨረራ አመንጪ ቁሶችን ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቡ አካላት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።


 

የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሠለሞን ጌታቸው በበኩላቸው ከጨረራ አመንጪዎች ጋር በተያያዘ ማሳወቅና ፈቃድ የማግኘት ግዴታዎች እንዲሁም ቁጥጥርና ክትትል ለማድረግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1025/2009 የሚያስፈጽም ደንብ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት ደንቡን ለማጸደቅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩንም አስታውቀዋል።

ባለስልጣኑ የሚወጡ ሕጎችን ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያግዙ ዝርዝር መመሪያዎችን እያወጣና ተግባራዊ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ የጨረራ ዝቃጭ ቁሶች ፖሊሲን በሚመለከት በረቂቅ ደረጃ የተዘጋጀ ሲሆን የባለድርሻ አካላት አስተያየት በግብዓትነት ተካቶበት ሥራ ላይ ለማዋል እየተሰራ ነው።

እንደ የጨረራ ህክምና ምርምራ መስጫን ጨምሮ ጨረራ አመንጪ መሳሪያዎች ያለ ፈቃድ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ከጉምሩክ ኮሚሽንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።


 

የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ፤ ባለስልጣኑ በሀገሪቱ ያሉ ጨረራ አመንጪ መሳሪያዎች በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውሉ የሚያደርገውን ቁጥጥር ማጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።

በተለይም ባለሥልጣኑ ሥራዎችን ለማከናወን ከተለያዩ ተቋማት ጋር ያደረገው ሥምምነት ወደ መሬት እንዲወርድ ሊሰራ እንደሚገባውም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም