የበቆሎ መዝሪያ ወቅት የደረሰብን በመሆኑ ምርጥ ዘር ፈጥኖ ሊቀርብልን ይገባል- የምሰራቅና ምእራብ ጎጃም ዞን አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የበቆሎ መዝሪያ ወቅት የደረሰብን በመሆኑ ምርጥ ዘር ፈጥኖ ሊቀርብልን ይገባል- የምሰራቅና ምእራብ ጎጃም ዞን አርሶ አደሮች
ባህር ዳር ፣ግንቦት 27/2015 (ኢዜአ) የበቆሎ መዝሪያ ወቅት እየደረሰብን በመሆኑ ምርጥ ዘር ፈጥኖ ሊቀርብልን ይገባል ሲሉ በአማራ ክልል የምእራብና ምሰራቅ ጎጃም ዞን አርደሶ አደሮች ጠየቁ ።
በክልሉ ለመኽር ወቀት የሚያገለግል ከ78 ሽህ ኩንታል በላይ የበቆሎ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማስረግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል ።
በአማራ ክልል ምእራብና ምስራቅ ጎጃም ዞኖች ነዋሪ የሆኑ አርሶ አደሮች ለኢዜአ እንደገለጹት በአካባቢው በመኽር ወቅት ቀድመው ከሚዘሩ ሰብሎች አንዱ በቆሎ ነው ።
አሁን ላይ እየጣለ ባለው ዝናብ ማሳቸውን ደጋግመው በማረስ በበቆሎ ዘር ለመሸፈን ዝግጅት ቢያደርጉም የምርጥ ዘር አቅርቦት ባለመጀመሩ ስጋት እንደሆነባቸው አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል።
በምእራብ ጎጃም ዞን የወንበርማ ወረዳ ማር ወለድ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ባዩ ተጃረ እንደገለጹት አንድ ሄክታር ማሳቸውን በበቆሎ ሰብል ለመሸፈን የእርሻ ስራ አከናውነዋል።
አካባቢው ደጋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከሚያዚያ ወር መግቢያ ጀምሮ በቆሎ ለመዝራት ማሳቸውን በማረስ ዝግጅት ያደረጉ ቢሆንም እስካሁን የዘር አቅርቦት ባለመጀመሩ ስጋት እንዳደረባቸው ገልፀዋል።
ለዘር ስራው የሚሆን የአፈር ማዳበሪያ በቀበሌያቸው የደረሰ ቢሆንም እስካሁን ምርጥ ዘር እንዳልቀረበና የፍላጎት ልየታም እልዳልተካሄደ አመልክተዋል።
ለህገ ወጥ ዘር አቅራቢዎች ከመጋለጣቸውና የዘር ወቅት ሳያልፍባቸው በፊት ምርጥ ዘር ፈጥኖ እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል።
በምርት ወቅቱ 4 ሄክታር ማሳቸውን በበቆሎ ዘር ለመሸፈን የእርሻ ስራ ማጠናቀቃቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አርሶ አደር ዳኛቸው በቀለ ናቸው።
ለበቆሎ ልማቱ 100 ኪሎ ግራም ምርጥ ዘር የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም እየቀረበ ባለመሆኑ የዘር ወቅቱ ሊያልፍ ይችላል የሚል ስጋት እንደፈጠረባቸው አመልክተዋል።
በምስራቅ ጎጃም ዞን ማቻከል ወረዳ የወላ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ለዓለም ይታየው በበኩላቸው ግማሽ ሄክታር መሬት በበቆ ዘር ለመሸፈን አቅደው ማሳቸውን ደጋግመው በማረስ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።
ቀደም ብሎ መጣል የጀመረው ዝናብ ለእርሻ ስራው ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቅሰው ከሳምንት በኋላ ዘር ለመዝራት ያሰቡ ቢሆንም እስካሁን ምርጥ ዘር ባለመቅረቡ ስጋት እንዳጋጠማቸው ገልፀዋል።
የዘር ወቅት ከማለፉ በፊትና በዘር ወቅት መጉላላት እንዳይገጥማቸው ምርጥ ዘር ከወዲሁ እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል።
በመኽር ወቅቱ በበቆሎ ሰብል ለሚያለሙት ግማሽ ሄክታር ማሳ ከ15 ኪሎ ግራም በላይ ምርጥ ዘር እንደሚያስፈልጋቸው የገለጹት ደግሞ በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤሌያስ ወረዳ የጠጠር ጥጃ ጎጥ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አተረፍ አንዷዓለም ናቸው።
ከሚያዚያ ወር መግቢያ ሳምንት ጀምሮ በቆሎ ለመዝራት የእርሻ ስራ ቢያጠናቅቁም እስካሁን የምርጥ ዘር አቅርቦት ባለመኖሩ ስጋት የፈጠረባቸው መሆኑን ጠቁመው “የሚመለከተው አካል የዘር ወቅቱ ከማለፉ በፊት ፈጥኖ ሊያቀርብ ይገባል” ሲሉ አመልክተዋል።
በምዕራብ ጎጃም ዞን የወንበርማ ወረዳ ግብርና ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ቢምረው የኔው ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ “በወረዳው በመኽር ወቅት ቀድሞ በበቆሎ ዘር ለሚሸፈነው መሬት 7 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ያስፈልጋል” ብለዋል።
የሚያስፈልገው የበቆሎ ምርጥ ዘር እሰካሁን አለመቅረቡ ትክከል መሆኑን ገልጸው ዘሩ በቅርብ ቀናት ውስጥ እንደሚቀርብ አመላክተዋል። "አርሶ አደሩ ያነሳው የስጋት ጥያቄ ትክክልና ተገቢ ነው" ያሉት ደግሞ የምስራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ሃላፊ ዘቶ ፈንታሁን ቸኮል ናቸው።
"ነገር ግን የክልሉ ግብርና ቢሮ የአርሶ አደሩን ጥያቄ ከግምት በማስገባት አፋጣኝ ምላሽ በመውሰዱ አቅራቢዎች ተለይተው ከነገ ጀምሮ ምርጥ ዘሩ ወደየ መጋዘኑ ይደርሳል" ብለዋል።
"በዞኑ በቆሎ ከጤፍና ስንዴ በመቀጠል በሦስተኛ ደረጃ በስፋት የሚለማ ሰብል በመሆኑ በሚቀጥሉት አራት ቀናት ውስጥ መርጥ ዘሩ በየአርሶ አደሩ እጅ ይገባል" ሲሉም አክለዋል።
በዞኑ በመኽር ወቅቱ 97 ሽህ ሄክታር መሬት በበቆሎ ሰብል እንደሚሸፈን ጠቅሰው የበቆሎ ምርጥ ዘሩ የዘር ወቅቱ ሳያልፍ በበቂ መጠን ስለሚቀርብ አርሶ አደሩ ተረጋግቶ እንዲወስድ አስገንዘበዋል ።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የግብርና ግብዓትና ገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ዳይሬክተር ወይዘሮ ሙሽራ ሲሳይ በበኩላቸው "በክልሉ 2015/16 ምርት ዘመን መኽር ወቅት 209 ሽህ ኩንታል የተለያየ የሰብል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ይደረጋል" ብለዋል።
በምርት ወቅቱ ተደራሽ ከሚደረገው ከአጠቃላይ ምርጥ ዘር ውስጥ 78 ሺህ ኩንታል የሚሆነው የበቆሎ ዘር መሆኑን ጠቅሰዋል።
የበቆሎ ምርጥ ዘሩ ለአርሶ አደሩ በቀጥታና በመደበኛ ግብይት ተደራሽ እንዲሆን የሚያስችል አሰራር ተመቻችቶ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
"የአካባቢውን የአየር ፀባይ ታሳቢ ያደረጉ ሊሙ፣ ቢኤች 660 እና ቢኤች 661 የተሰኙ የበቆሎ ምርጥ ዘሮች ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ ስራዎች እየተከናወኑ ነው" ሲሉም አክለዋል።
ምርጥ ዘሩ በተለይም ቀድመው ለሚዘሩ ደጋማ አካባቢዎች በወቅቱ እንዲደርስላቸው ታስቦ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ሲሆን በተያዘው ሳምንት ውስጥ አቅራቢዎች በየወረዳዎቹ ዘሩን ተደራሽ እንዲያደርጉ የሚያስችላቸውን ምደባ መካሄዱን ተናግረዋል።
ምርጥ ዘሩ ለአርሶ አደሩ በወቅቱ እንዲደርስ የጠቀሱት ዳይሬክተሯ የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር አለመኖሩንም አረጋግጠዋል።
በክልሉ በ2014/15 ምርት ዘመን መኽር ወቅት 160 ሺህ ኩንታል የተለያየ የሰብል ምርጥ ዘር ቀርቦ ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቶ ጥቅም ላይ መዋሉን ዳይሬክተሯ አስታውሰዋል።
በክልሉ በ2015/16 የምርት ዘመን ከ4 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር በላይ ማሳ በተለያዩ ሰብሎች ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።