በውጭ ሀገራት ሲሰጥ የቆየው የሕክምና ባለሙያዎች የብቃት ማረጋገጫ ፈተና በሀገር ውስጥ መስጠት ሊጀመር ነው - ኢዜአ አማርኛ
በውጭ ሀገራት ሲሰጥ የቆየው የሕክምና ባለሙያዎች የብቃት ማረጋገጫ ፈተና በሀገር ውስጥ መስጠት ሊጀመር ነው
አዲስ አበባ መጋቢት 27/2015(ኢዜአ)፦ በውጭ ሀገራት ሲሰጥ የቆየው የሕክምና ባለሙያዎች የብቃት ማረጋገጫ ፈተና በሀገር ውስጥ መስጠት ሊጀመር መሆኑ ተገለጸ።
ፈተናውን በሀገር ውስጥ መስጠት የሚያስችል ስምምነት ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሄዷል።
በሕክምና ትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ዕውቅና አሰጣጥ ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት መድረክ በአዲስ አበባ ተካሄዷል።
መድረኩ የተዘጋጀው በጤና ሚኒስቴር፣ በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የምክክር መድረክ እና በ 'ፒዩፕል ቱ ፒዩፕል' የተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በትብብር ነው።
በሀገር ውስጥ እንደሚሰጥ የተገለጸው የሕክምና ባለሙያዎች የብቃት ማረጋገጫ ፈተና የሕክምና ባለሙያዎች በውጭ አገራት እንዲሰሩ ዕድል የሚያሰፋ፣ የውጭ ምንዛሬ ወጪን የሚቀንስ ብሎም በትምህርት ጥራት ላይ አዎንታዊ ሚና የሚያመጣ መሆኑም ተገልጿል።
ዓለም አቀፍ የሕክምና ተማሪዎች የብቃት ማረጋገጫ ፈተናን በሀገር ውስጥ መስጠት የሚያስችል ስምምነት በጤና ሚኒስቴር፣ በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የምክክር መድረክ እና በ 'ፒዩፕል ቱ ፒዩፕል' የተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ተፈራርመዋል።
በኢትዮጵያ በሕክምና ትምህርት ጥራትን ለማሻሻል፣ የተቋማቱን ብቃት ለማረጋገጥና ዕውቅና እንዲኖራቸው ለማስቻል ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገልጸዋል።
ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ምሁራን አባላትን ያቀፈውና በትምህርት ዘርፍ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት፣ በጤናው መስክም ድጋፍ እና የማማከር ስራዎችን የሚያከናውነው የ'ፒፕል ቱ ፒፕል' አንዱ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ስምምነቱ የሕክምና ትምህርት ተቋማት በዓለም አቀፍ ደረጃ የብቃት ማረጋገጫ ዕውቅና እንዲኖራቸው እንዲሁም ብቁ ሐኪሞች ለማፍራት ያለመ ነው ብለዋል።
በውጭ ሀገራት ሲሰጥ የቆየውን የሐኪሞች የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ፈተና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሚቋቋም የምዘና ማዕከል አማካኝነት እንዲሰጥ ማስቻል መሆኑን ነው ዶክትር ሊያ ያመለከቱት።
የሕክምና ባለሙያዎች የብቃት ማረጋገጫ ፈተና በአገር ውስጥ መሰጠቱ ባለሙያዎች በውጭ አገራት እንዲሰሩ ዕድል የሚያሰፋ፣ የውጭ ምንዛሬ ወጪን የሚቀንስ ብሎም በትምህርት ጥራት አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
የ'ፒፕል ቱ ፒፕል' መስራችና ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር እናውጋው መሐሪ እንዳሉት፤ ከ100ሺህ በላይ የዳያስፖራ አባላት ያሉት ድርጅቱ ዓለም አቀፍና ሀገር ውስጥ ድርጅቶችን በማቀናጀት የሰዎችን ችግር ለመፍታት ዓላማ ይዞ ሲሰራ ቆይቷል።
ኤች አይ ቪ/ኤድስ ወረርሽኝን ተከትሎ እ.አ.አ በ1999 በአሜሪካ የተቋቋመው ድርጅቱ በኢትዮጵያ በትምህርት እና የጤናው ዘርፍን ለማሻሻል ዕውቀትና ቴክኖሎጂን በማጋራት አበክሮ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በአገር ውስጥ ለመስጠት የተደረሰው ስምምነትም የብቃት ማረጋገጫ ፈተናው አሜሪካ ባሉ ባለሙያዎች እንደሚሰጥ ገልጸው፤ ከሦስት ወራት በኋላ ስራ ለማስጀመር ዕቅድ እንዳላቸው ነው ፕሮፌሰር እናውጋው የጠቆሙት።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የምክክር መድረክ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው የሙያ ጥራት ማረጋገጫ ዓለም አቀፍ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
የጤናውን ዘርፍ ጨምሮ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰው፤ የትምህርት ተቋማት ብቃት ማረጋገጫ እንዲኖራቸው ማስቻልና ሐኪሞች የብቃት ማረጋገጫ ፈተና በቀላሉ እንዲያገኙ ማድረግ ለአገር ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ተግባር ይግዛው፣ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዑጁሉ ኡኮክና የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ጉማ አዱኛ የብቃት ማረጋገጫ ፈተናው "በአገር ውስጥ ከተሰጠ ለሕክምና ተማሪዎች ትልቅ ብስራት ነው" ብለዋል።