ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ተቋማዊ ማድረግ የሚያስችል አሰራር ማሻሻያ እየተደረገ ነው - የኢንዱስትሪ ሚኒስትር

አዲስ አበባ መጋቢት 27/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን  በሀገር አቀፍ ደረጃ ተቋማዊ ለማድረግ የሚያስችል የአሰራር ማሻሻያ እየተደረገ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገለጹ፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄን ውጤታማ ማድረግ በሚያስችል ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የፌደራል ክላስተር ኮሚቴዎች የሚኖራቸውን ሚና በሚመለከት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡


 

በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪውን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ያለመ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በ2014 ዓ.ም በይፋ መጀመሩ ይታወቃል፡፡

የኢንዱስትሪ  ሚኒስትር መላኩ አለበል በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ንቅናቄውን ተቋማዊና ዘላቂ ለማድረግ የዘርፉ ተዋንያንን ትብብርና ቅንጅት ይጠይቃል፡፡

በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች በተናበበ መልኩ መፍታት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት መሻሻል ሚናው የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአምራቹን ዘርፍ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የተቋማት ጥምረት ለውጦችን ቢያመጣም ዘርፉ የሚጠበቅበትን ያክል አስተዋጽኦ ከማድረግ አኳያ ግን በቂ አይደለም ብለዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ዘርፉን ዘላቂ እና ወጥ በሆነ መልኩ እንዲከናወን የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ማጎልበት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ንቅናቄውን ተቋማዊ ለማድረግ የአሰራር ማሻሻያዎች  እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተለያየ ዘርፍ ላይ የሚገኙ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም በማጎልበት የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የዘርፉ ተዋንያን ተሳትፎ የጎላ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማሳለጥ በኢንዱስትሪ ዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን መፍታት ለነገ የማይባል መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ከመንግስት ጥረት በተጨማሪ የግል ተቋማት ንቁ ተሳታፊና በትብብር የሚሰሩ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አስፋው አበበ፤ ንቅናቄውን ውጤታማ ለማድረግ በአራት ክላስተር የተከፈለ ኮሚቴ መዋቀሩን ገልፀዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አካላት የሚያነሱትን የመሰረተ ልማት ማሟላት፣ የግብዓት አቅርቦትን ማሻሻል፣ የፋይናንስ ጥያቄዎችን መፍታት ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለዘርፉ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በጥናት ላይ የተመሰረተ መፍትሄ መስጠትና ኢንቨስትመንትን መሳብ የሚያግዙ ኮሚቴዎችም ተቋቁመዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዋነኛ አላማ በዘርፉ ያጋጠሙ ችግሮችን መፍታት፣ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር እንዲሁም የህብረተሰብ ንቅናቄን መፍጠር መሆኑ ይታወቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም