ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ የጎዳና ላይ የኢፍጣር መርሃ ግብር የፊታችን ቅዳሜ ይካሄዳል

አዲስ አበባ መጋቢት 27/2015 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የጎዳና ላይ የኢፍጣር መርሃ-ግብር የፊታችን ቅዳሜ (መጋቢት 30 ቀን 2015 ዓ.ም) ይካሄዳል።

በዕለቱ በድርቅና በተለያዩ ምክንያቶች ለተፈናቀሉና ችግር ለገጠማቸው ወገኖች ድጋፍ ይሰባሰባል ተብሏል።  

የኢፍጣር ፕሮግራሙ ጊዜያዊ አስተባባሪ አቶ ፈይሰል ከማል መርሃ-ግብሩን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።

  በመግላጫቸውም የጎዳና ላይ ፕሮግራም "ኢፍጣራችን ለወገኖቻችን" በሚል መሪ ሃሳብ የፊታችን ቅዳሜ መጋቢት 30 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የሚከናወን መሆኑን ተናግረዋል።  

የጎዳና ላይ ኢፍጣሩ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳይ ከፍተኛ ምክር ቤት ከሃላል ፕሮሞሽንና ነጃሺ  የበጎ አድራጎት ማኅበር ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑንም  ገልጸዋል።

  በኢትዮጵያ ለሦስተኛ ጊዜ የሚካሄድ ታላቅ የኢፍጣር ፕሮግራም መሆኑን ጠቅሰው፤ የመተባበር እና የመተጋገዝ የኢትዮጵያን እሴት በሚያጠናክር መልኩ የሚከናወን መርሃ-ግብር መሆኑንም ተናግረዋል።

  በዕለቱ በድርቅና በተለያዩ ምክንያቶች ለተፈናቀሉና ችግር ለገጠማቸው ወገኖች ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራም ይከናወናል ብለዋል።  

  የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳይ ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ሸኸ ሁሴን በሽር እና የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ልዩ አማካሪ ዑስታዝ አቡበክር አህመድ፤ የመርሃ ግብሩን አስፈላጊነት በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋለ።

    የጎዳና ላይ ኢፍጣሩ ዋነኛ ዓላማ አቅም የሌላቸውን ወገኖችን ለማስፈጠር እና አብሮነትን ለማጠናከር ያለመ መሆኑን አስረድተዋል፡፡  

በመርሃ-ግብሩ ላይ የእምነቱ አባቶች፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና በርካታ የእምነቱ ተከታዮች የሚሳተፉ ይሆናል።  

የኢፍጣር ሥነ-ሥርዓቱን የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ከሀላል ፕሮሞሽንና ከነጃሺ በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን እንደሚያካሂዱት ተገልጿል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም