በኢትዮጵያ የቴኳንዶ ስፖርት ክለብ አለመኖር ለስፖርቱ መስፋፋትና እድገት ማነቆ ሆኗል-ስፖርተኞች - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የቴኳንዶ ስፖርት ክለብ አለመኖር ለስፖርቱ መስፋፋትና እድገት ማነቆ ሆኗል-ስፖርተኞች

አዲስ አበባ መጋቢት 27/2015(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የቴኳንዶ ስፖርት ክለብ አለመኖር ለስፖርቱ መስፋፋትና እድገት ማነቆ መሆኑን የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርተኞች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት ፌዴሬሽን በበኩሉ፤ በቀጣይ ክለቦችን ለመመስረት ሥራዎች ተጀምረዋል ብሏል።
የቴኳንዶ ስፖርት በዋናነት ሙሉ ሰውነትን የሚያንቀሳቅስ ቢሆንም የእጅና እግር ጥምረትን በማቀናጀት በልዩ ጥበብና ቅንጅት የሚሰራ ተወዳጅ ስፖርት ነው።
ከሕጻንነት እድሜ ጀምሮ በተለያዩ የእድሜ ክልሎች የሚዘወተር መሆኑም ይታወቃል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ የቴኳንዶ ስፖርት ክለብ አለመኖር ለዘርፉ መስፋፋትና እድገት ማነቆ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የዘርፉ ስፖርተኞች ገልጸዋል።
ቴኳንዶ ወጣቶችን በጥሩ ስነ-ምግባር የሚገራ የስፖርት ዘርፍ ቢሆንም በኢትዮጵያ የሚገባውን ያክል ትኩረት የተሰጠው አለመሆኑን አትሌት ጸባኦት ጎሳዬ ገልጻለች።
ስፖርቱ በታዳጊዎች እንዳለው ተወዳጅነትና ተሳትፎ የክለቦች አለመኖር ዘርፉን የጎዳው ስለመሆኑም ተናግራለች።
ሌላኛው የቴኳንዷ ስፖርተኛ አብዱራህማን ሰፋ፤ ቴኳንዶ ከአትሌቲክስ ስፖርት ቀጥሎ በተለያዩ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ውድድሮች ኢትዮጵያ ጥሩ ውጤት የምታስመዘግብበት የስፖርት ዓይነት አንደኛው ነው።
በሌሎች ሀገራት እድሜያቸው 40 ዓመትና ከዚያም በላይ እስከሚሆን ውድድር ላይ እንደሚቆዩ በማስታወስ፤ በኢትዮጵያ ግን 30 ዓመት ሳይሞላቸው ከውድድር እንደሚርቁም ነው የገለጸው።
የችግሩ ምክንያትም በዋናነት ስፖርተኞች በክለቦች ስለማይታቀፉ መሆኑን አብዱራህማን ተናግሯል።
ታዳጊዎችን ማብቃት ላይ በትኩረት ከተሰራ አገርን የሚወክሉ በርካታ ተወዳዳሪዎችን ማፍራት የሚቻልበት የስፖርት ዓይነት መሆኑን የገለጹት ደግሞ አትሌት ዘሪሁን ዘውዴና ማስተር ማርሸት ዘውዱ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት ፌዴሬሽን በበኩሉ፤ ለዘርፉ እድገት በማሰብ በቀጣይ ክለቦችን ለመመስረት ስራዎች ተጀምረዋል ብሏል።
የፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ፍቅሩ ተቋም፤ ስፖርቱን ለማሳደግ ከሚያግዙ ተግባራት አንዱ ክለቦች እንዲኖሩ ማድረግ መሆኑን በስራ አስፈጻሚ ደረጃ ታምኖበት ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።
ከተመረጡ ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ክለብ እንዲይዙ መግባባት ላይ ስለመደረሱም ጠቅሰዋል።
ከክለቦች ማቋቋም ባለፈ የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማድረግ ከወዲሁ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።