ለጤና ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ የብቃት ማረጋገጫ ፈተና በአገር ውስጥ ለመስጠት የሚያስችል ሥምምነት ተፈረመ - ኢዜአ አማርኛ
ለጤና ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ የብቃት ማረጋገጫ ፈተና በአገር ውስጥ ለመስጠት የሚያስችል ሥምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ መጋቢት 27/2015(ኢዜአ)፦ ለኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ የብቃት ማረጋገጫ ፈተና በአገር ውስጥ ለመስጠት የሚያስችል የመግባቢያ ሥምምነት ተፈረመ።
ሥምምነቱ የጤና ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም የሰዎች ለሰዎች የተሰኘው የረድኤት ድርጅት ፈርመውታል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ሥምምነቱ የብቃት ማረጋገጫ ዕውቅና ፈተናው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት እንዲሰጥ ያስችላል።
ይህም ኢትዮጵያ ለፈተናው የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት ያግዛል ነው ያሉት።
ዓለም አቀፍ የብቃት ማረጋገጫ ፈተናው በሀገር ውስጥ መሰጠቱ የጤና ባለሙያዎች ወደ ውጭ አገራት በመሄድ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ዕድል በቀላሉ እንዲያገኙ ያግዛል ብለዋል።
የጤና ትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ መንግሥት የሚሰራውን ሥራ እንደሚያግዝም ዶክተር ሊያ ገልጸዋል።
የ"ሰዎች ለሰዎች" ድርጅት ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር እናውጋው መሃሪ ድርጅቱ በትምህርትና በጤና ዘርፍ ዕውቀትና ቴክኖሎጂ በማጋራት አገር በቀል መፍትሔ ማፍለቅ ላይ እየሰራ ነው ብለዋል።
አገርን ወደ ፊት ለማራመድ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥቅሟን ለማስከበር የተማረና ብቁ የሰው ኃይል ያስፈልጋል ለዚህ በትብብር መሥራት ይገባል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የምክክር መድረክ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና የሙያ ጥራት ማረጋገጫ ዓለም አቀፍ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።