ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማሳለጥ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ላይ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን መፍታት ይገባል--አቶ መላኩ አለበል

 

አዲስ አበባ መጋቢት 27/2015 (ኢዜአ)፦ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማሳለጥ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ላይ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን መፍታት አለብን ሲሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።

ሚንስቴሩ የኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄን ውጤታማ ማድረግ በሚያስችሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የፌዴራል ክላስተር ኮሚቴዎች የሚኖራቸውን ሚና በሚመለከት በተዘጋጀ ሰነድ ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየተወያየ ይገኛል።

በዚሁ ወቅት ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ለመፍታት በዘርፉ ያለን ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተን ልንሰራ ይገባል ብለዋል።

ሚኒስቴሩ ኢንዱስትሪ ዘርፉን በማሳደግ የሀገሪቱን ምርትና ምርታማነት ለማሻሻል፣ ማነቆዎችን ለመቅረፍ ከባለፈው በጀት ዓመት ጀምሮ ኢትዮጵያ ታምርት በሚል ንቅናቄ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ያከናወናቸው ተግባራት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣታቸውን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተቋማዊ በሆነ መልኩ ብሎም በዘላቂነት ለማስቀጠል የተለያዩ የፌዴራል ተቋማትና የባለሀብቶች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልፀው ንቅናቄውን ውጤታማ ለማድረግ የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊጫወቱ ይገባል ብለዋል።

ለአብነትም የመሰረተ ልማት እና የግብዓት ችግሮችን መቅረፍ ተጠቃሽ ናቸው ሲሉም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም