ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የምርት ጥራት ምርመራና ሰርቲፊኬሽን አገልግሎት በጅማና ሃዋሳ መስጠት ሊጀምር ነው

አዲስ አበባ መጋቢት 26/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የምርት ጥራት ምርመራና ሰርቲፊኬሽን አገልግሎት በጅማና ሃዋሳ መስጠት ሊጀምር መሆኑን የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሻፊ ኡመር ገለጹ።

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሻፊ ኡመር ዛሬ በሰጡት መግለጫ የምርት ጥራት ምርመራና ሰርቲፊኬሽን አገልግሎት በጅማና ሃዋሳ ይጀመራል ብለዋል።   

ይህንንም ተከትሎ በጅማ መጋቢት 28 እንደዚሁም በሃዋሳ ደግሞ ሚያዝያ 3 ቀን 2015 አገልግሎቱ በይፋ ተጀምሮ ወደ ሥራ እንደሚገባ ነው ያስረዱት። 


 

የማዕከላቱ ሥራ መጀመር የቡና አምራቹ፣ አልሚውና አቅራቢው እንዲሁም ላኪው ይደርስበት የነበረውን እንግልት፣ ከፍተኛ ወጪና የጊዜ ብክነት ያስቀራል ብለዋል። 

ያም ብቻ ሳይሆን ቡናን ከአንድ ሥፍራ ወደ ሌላ ሥፍራ በማጓጓዝ የሚከሰተውን የጥራት መጓደልና የምርት ብክነትን በመቀነስ አስተዋጽዖ የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።  

የሚመረቱ የቡና ምርቶች በቀጥታ ወደ ዓለም ገበያ ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረትም በእጅጉ እንደሚያግዝም ነው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት። 

ማዕከላቱ አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማትና ቁሳቁሶችን የማሟላት እንዲሁም ባለሙያዎችን የመቅጠር ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።

በቀጣይ ዓመት ደግሞ በሌሎች አካባቢዎች ተጨማሪ ማዕከላት በመገንባት አገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን ጥቅም ከፍ ለማድረግ ይሰራል ነው ያሉት።   

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የጥራት ምርመራና ሰርቲፊኬሽን አገልግሎት በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ማዕከላት ብቻ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር ይታወሳል።

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም